በስመ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
- *በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ
- *ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር በከተማ የምትኖሩ
- *የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ
- *በሕማም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ
- *እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
እንኳን ለ2004 ዓ.ም. የጌታችን፤ የአምላካችንና የመድሃታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ፡፡
‹‹ወበዝንቱ ተዐውቀ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር ላዕሌነ እስመ ለወልዱ ዋሕድ ፈነወ ውስተ ዓለም ከመእንሕየው ቦቱ›› በእርሱ ቤዛነት እንድን ዘንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮልናል፤ እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ፍቅር በዚህ አውቀናል›› 1 ዮሐ 4፡9
እግዚአብሔር ከፍጡራን ሁሉ የተለየና ከአእምሮ በላይ የሆነ መለኮታዊ ሀይል ያለው አምላክ በመሆኑ የባህርዩን ጥልቅነት በምልኣት ማወቅ ፈጽሞ የማይቻል ቢሆንም እርሱ ራሱ በገለጸልን መጠን የተወሰኑ ነገሮችን እናዉቃለን፡፡
እግዚአብሔር ለፍጡራን ያለው የፍቅር ባህርይ እጅግ ጥልቅና የማይናወጥ መሆኑ የተገለጸበት ቀን ቢኖር እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ሥጋ ለብሶ በቤተልሔም የተወለደበት ቀን ነው፡፡
ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሕር ፍቅር ነው›› ብሎ ምልአተ ፍቅሩን ካስረዳ በኋላ በማስረጃ ሲያብራራ ‹‹ቤዛ ሆኖ የሰውን ልጅ ያድን ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮአልና ፍቅሩን በዚህ አውቀናል›› ይላል፡፡ እግዚአብሔር በልጁ መሥዋዕትነት ዓለምን ለማዳን ያደረገው ፍቅር ከሌላው ሁሉ የበለጠ በመሆኑ ልቆ ተነገረ እንጂ የእግዚአብሔር ፍቅር ከፍጡራን የተለየበት ጊዜ እንደሌለ ሁላችንም እናዉቃለን፤ በስፋት ልንገነዘብም ይገባናል፡፡
የእግዚአብሔር ፍቅር በዓለም ላይ በምልኣት ባይኖር ኖሮ ሰማይና ምድር እንደዚሁም በውስጣቸው የሚገኙ የሚያዩና የማያዩ ፍጥረታት በሙሉ ሕገ ተፈጥሮኣቸውንና ሥርዓተ ምሕዋራቸውን ጠብቀው መኖር አይችሉም ነበር፡፡
ሰዎችም ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ውሣጣዊና ውጫዊ ምግብን ማግኘት አይችሉም ነበር፡፡
እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ በመሆኑ ጥፋተኛውንና እውነተኛዉን ሳይለይ ፍጡራንን ሁሉ በፍቅር ይመግባል፤ ይመራል፤ ይቆጣጠራል፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅር ምን ያህል ሰፊና ምሉእ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
እግዚአብሔር አንዳችም ሳያጎድልበት ሰው በራሱ የተሳሳተ ምኞት ከእግዚአብሔር ፍቅር ቢለይም የሰው በደል በእግዚአብሔር ፍቅር ይሸነፋል እንጂ፤ የእግዚአብሔር ፍቅር በሰው በደል ሊሸነፍ ከቶ የማይቻል ነውና የእግዚአብሔር ፍቅር የሰውን በደል ሲያሸንፍ በፍቅረ እግዚአብሔር ተሰባስበው የተገናኙ ሰማያውያንና ምድራውያን ፍጥረታት በአንድነት ‹‹ለእግዚአብሔር በሰማያት ክብር ተደረገ፤ በምድርም ሰላም ሆነ፤ ለሰውም በጎ ፈቃድ ተሰጠ›› እያሉ በቤተልሔም ከተማ ዘመሩ፡፡ (ሉቃስ 2፡14)
እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በፍቅር ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ በዛሬው ቀን በቤተልሔም ውስጥ ለዓለም የሰጠው ስጦታ እጅግ በጣም የላቀ ነው፡፡ ምክንያትም ሌሎች ስጦታዎች ከፍጥረቶቹ የሚገኙ የፍጥረት ውጤት ስጦታዎች ሲሆኑ የቤተልሔም ስጦታ ግን አንድ ልጁን ነውና፡፡
በመሆኑም በዛሬዋ ዕለት በሆነው ነገር እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍጹም ፍቅር ምን ያህል እንደሆነ በሚገባ ለማወቅ ችለናል፤ ልብ እንበል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ!
የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጸው፤
- *የሰው ዘር በአጠቃላይ በአዳም በደል ምክንያት ለሞትና ለአሣር እንደተዳረገ ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት ምክንያት የሰውን ዘር ሁሉ ለማዳን፤
- *እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው የላቀ ነገር ቢኖር የእርስ በርስ መፋቀር እንደሆነ ለማስረዳት
- *በኃጢአት ምክንያት ያጣነውን በእግዚአብሔር መንግስት በክብርና በዘላለማዊ ሕይወት የመኖር ዕድል ለማስመለስ ነው፡፡
በዛሬው ዕለት በቤተልሔም የተወለደው ጌታችን አምላካችን መድሃኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ሰውን ለፍጹም ምሕረት ለማብቃት በመሆኑና ምሕረቱንም በብዛት ስላፈሰሰልን ከጌታ ልደት ወዲህ ያለው ዘመን ዓመተ ምሕረት፤ ማለትም የምሕረት ዘመን ተብሎ ይታወቃል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ!
እግዚአብሔር እኛን ይህን ያህል ከወደደን እኛም እርስ በርስሳችን ልንዋደድ ይገባናል፤ ከልደተ ክርስቶስ የምንማረው ትምህርት፤ ወገንን ሁሉ ማለትም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን የሰው ዘር ሁሉ መውደድና መርዳት ነው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹መሥዋዕትን ያይደለ ምሕረትን እወዳለሁ፤ እነሆ አዲስ ትእዛዝ ሰጣችኋለሁ፤ እርሱም እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ነው፡፡›› ብሎ እንዳስተማረን በፍቅር እየኖርን ችግረኞችን መርዳት ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔር መሆናችንን ሰውን በመውደድና በመርዳት መግለጽ ይኖርብናል፡፡
ባለንበት ዘመን በተለያየ ምክንያት እናትና አባትን ያጡ፤ የወገንን ፍቅርና እንክብካቤ የሚሹ ብዙ የእግዚአብሔር ልጆች በየሰፈሩ አሉ፡፡ ለበዓል መዋያ ያዘጋጀነውን ህብስተ በረከት ከተቸገሩት ሕጻናትና፤ የሚላስ የሚቀመስ ካጡ ወገኖች ጋር በህብረት መመገብ ይገባናል፡፡ ይህን ስናደርግ በፍጹም ፍቅሩ የወደደንን እግዚአብሔር በቤታችን ውስጥ የጋበዝን እንደሆነ እርግጠኞች መሆን አለብን፡፡ ‹‹ ተርቤ አብልታችሁኛል ኑ ወደ እኔ›› የሚል ቃል ኪዳን እንዳለበትም እናስታውስ፡፡
በሌላ በኩል በልዩ ልዩ በሽታ ተይዘው መዳንን በመሻት በየሆስፒታሉና በየሰፈሩ የሚገኙ ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ በእነዚህ ወገኖች አድልዎና ማግለል ሳናደርግ ማስታመምና አቅማችን በፈቀደ መጠን እነርሱን ለማገዝ መረባረብ ምሕረትን የሚያስገኝልን እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡ ‹‹ብታመም ጠይቃችሁኛልና መንግሥተ ሰማያትን ትወርሱ ዘንድ ወደ እኔ ኑ›› የሚል ቃል ኪዳን እንዳለበትም አንዘንጋ፡፡
መማር የሚያስፈልጋቸው ነገር ግን አቅመቢስ በመሆናቸው በአልባሌ ቦታ ጊዜአቸውን የሚያባክኑ ተገቢውን እርዳታ በማሟላት ብቁ ዜጋ ማድረግ፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ!
የኑሮ መጓደል በየትኛውም ክፍለ ዓለም ያለ ቢሆንም ሌት ተቀን ጠንክረው በመሥራታቸው በተሻለ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኑሮ የሚኖሩ ሀገሮች እንዳሉ እናውቃለን፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያንም አሁን በተጀመረው የልማት ጎዳና በመሮጥ ሁላችን ለሥራ ብቻ ከተሰለፍን ያለብን ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየተወገዱ፤ በሀገራችንም እንደበለፀጉት ሀገራት በልማት አድጋ፤ ሕጻናት በእንክብካቤ በእውቀት የሚያድጉባት፤ አረጋውያንና አረጋውያት የተቸገሩ ወገኖች በማህበራዊ ተቅዋማት የሚረዱባትና የሚከበሩባት፤ በሁሉም መስክ ዜጎች በደስታ የሚኖሩባት አገር ማድረግ እንደምንችል ጥርጥር የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድና ፍላጎትም ይህ ነው፡፡
ስለሆነም የተጀመሩና ሊጀመሩ ተቃርበው ያሉ ግዙፋን ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች የሀገራችን የድህነት ገጽ በመቀየር፤ ከበለጸጉ የዓለም ሀገራት ጎን በእኩልነት በክብር እንድትሰለፍ የሚያደርጉ፤ የሕብረተሰባችንን የዘመናት ችግር በአስተማማኝ ሁኔታ የሚቀንሱ መሆናቸው የታመነ ስለሆነና በሥራም የተረጋገጠ ስልሆነ ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ ለራሱና ለራሱ ሲል ከልማታዊ መንግሥታችን ጎን በመሰለፍ የልማት ሥራውን በየዘርፉ እንዲያፋጥን በእግዚአብሔር ስም መልዕክታችንን እንናስተላልፋለን፡፡
-
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ሕዝባችንንም ይቀድስ አሜን!
-
አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) ቀዳማዊ ፓትርያርክ
-
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
-
ሊቀ ጳጳስ ዘአኹስም
-
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
-
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት
-
የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት
-
ታህሳስ 28 ቀን 2004 ዓ.ም.

