የዓለም አብያተ ክርስቲያናት የኤክስኪዩቲቭ ኮሚቴ ጉባዔ ለመጀመሪያ ግዜ በኢትዮጵያ ተካሄደ
ከመስከረም 1-5 ቀን 2004 ዓ.ም የተካሄደው ይህ ጉባዔ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ መክፈቻ ንግግር ተከፍቱዋል፡፡
ክቡራን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት የኤክስኪዩቲቭ ኮሚቴ አባላት!
ወደ አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ እንኳን በደኅና መጣችሁ!
በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ ቆይታችሁ ሥራችሁ፣ ጉባኤያችሁ የተቃና፣ ያማረ፣ የሰመረ እንዲሆን እንመኛለን፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ በዓባይ ሸለቆ ዙሪያ በቀይ ባሕር አካባቢ የምትገኝ ጥንታዊት ታሪካዊት የክርስትና ሀገር ናት ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክርስትና በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ቁጥር 26-40 ያለው እንደሚናገረው በዘመነ ሐዋርያት በ34 ዓ.ም. ተመሥርቶ በየጊዜው እድገትን እያገኘ የመጣ ነው ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊት፣ ሐዋርያዊት ብሔራዊት በመሆኗ የኅብረተሰብኡን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማሟላት የሕዝቡ የሥራ ተካፋይ ሁና ኖራለች፤ አሁንም ሆነ ወደፊት በዚሁ ዓይነት ሥራዋን ትቀጥላለች ፡፡
ታሪክ እንደሚመሰክረው ቤተ ክርስቲያኒቱ በረጅሙ የታሪክ ዘመኗ የኢትዮጵያ ሕዝብ በክፉውም ሆነ በደጉ ዘመን ተከባብሮ፣ ተባብሮ በሰላም በፍቅር፣ በአንድነት፣ በመግባባት እንዲኖር ስታስተምር የኖረች፣ ያለች የምትኖር ናት ፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን በሃያኛው መቶ ዓመት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበርን ከመሠረቱት አንዷና የመጀመሪያዋ ናት፤ የመላ አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት መሥራች አባልም ናት፤ በመሥራችነቷም አገልግሎቷንና ግዴታዋን ስትፈጽም ቆይታለች ፡፡
እንደአገልግሎቷም ጥንካሬ በየሰባት ዓመቱ የሚደረገው የድርጅቱ ጀነራል አሴምብሊ በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ እንዲሆን በተደጋጋሚ ጥረትን አድርገን በተለያየ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፤ ወደፊት የጀነራል አሴምብሊው ጉባኤ በአዲስ አበባ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን ፡፡
ክቡራን እንግዶቻችን! የዓለም አብያተ ክርስቲያናት የኤክስኪዩቲቭ ኮሚቴ ስብሰባ በዚህ በአዲስ አበባ በመደረጉ ደስ ብሎናል፤ እንኳን በደኅና መጣችሁ ፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ጉባኤያችሁን፣ ስብሰባችሁን ይባርክ ይቀድስ ፡፡
እዚህ በመጫን ፎቶግራፍ ይመልከቱ፡፡




