የአጽዋማት ሥርዐት
ክፍል ሁለት
እነርሱም
ሀ. የመጀመሪያው ጾም፣ ዐቢይ ጾም ወይም ሁዳዴ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጦመው የአርባ ቀን ጦም ነው፡፡ (ማቴ፡4፣1) ምእመናን ጌታቸው ያደረገውን ምሳሌ ተከትለው ይጦሙታል፡፡ ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት (55 ቀኖች) አሉት፡፡ ከእነዚህም ቀኖች ውስጥ ሰባት ቅዳሜ ስምንት እሑድ ይገኛሉ፡፡ ዐሥራ አምስት ቀን ማለት ነው፡፡ ከጥሉላት እንጂ ከእህልና ከውሃ ስለማይጦም የጦሙ ወራት አርባ ቀን ብቻ ነው፡፡ ይህም በጥንታዊትዋ ቤተ ክርስቲያን የነበረ ሥርዐት ነው፡፡ ለምሳሌ በ384 ገደማ ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም ከእስፓኝ ወደ ኢየሩሳሌም ረዥም ጉዞ የሄደችው (Egeria) ኤጌሪያ የተባለችው ሴት የተሳላሚ ጉዞ በሚለው መጽሐፏ (Peregrinatioed Loca sancta) እንደጐበኘችና የጥንት ክርስቲያኖችም በዚህ አቈጣጠር ሲቈጥሩ ማየቷን ጽፋለች፤ የቆጵሮሱ ኤጲስ ቆጶስ ኤጲፋንዮስም በዚህ አቈጣጠር ይቈጥር ነበር ፡፡ (ፒ.ጂ.42 ሽህ 828) ሌሎች ደግሞ የመጀመሪያውንና የመጨረሻውን ሳምንት ለይተው ይቈጥራሉ፡፡ ለምሳሌም የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ሕርቃል /ኤራቅሊዮስ/ የቢዛንታይን ንጉሥ ነበር፡፡ (714 ዓ.ም.) ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበት ምክንያት አለው፤ በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ እርሱ ወደፋርስ ዘምቶ መስቀሉን ከእነርሱ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶአል፡፡ በዚህ ምክንያት ክርስቲያኖች ደስ ብሎአቸው ለስሙ መታሰቢያ ይህን የጾም ሳምንት በቀኖና ውስጥ አስገቡለት እየተባለ ይነገራል፡፡ ግሪኮች ግን ጾመ ሕርቃል የሚባለውን ነገር አያውቁም፤ በዚህ ሳምንት ከእንቁላል፣ ከአይብና ከዓሣ በቀር ሥጋ አይበላም ክልክል ነው፡፡ ጾም መሆኑንም ይናገራሉ፤ ከላይ የተጠቀሱትን መባልዕት መብላታቸውም በተድላ በደስታ የሰነበተ ሰውነታቸው ወዲያው በጾም ሲደርቅ በሽታ እንዳያመጣባቸው ለጥንቃቄ ነው ይላሉ፡፡ የሳምንቱንም ስም "የአይብ ሳምንት ወይም ነጭ ጾም" ይሉታል፡፡
የመጨረሻው ሳምንት ሕማማት ነው፤ ሐዋርያት የጌታችን መከራ መስቀል እያሰቡ የጦሙት ነው ይላሉ፤ ያም ሆነ ይህ ሁሉም ከዐቢይ ጾም ጋር እንደ መርገፍና እንደ እጀታ ስለተያያዘ ከዐቢይ ጾም ይቈጠራል፡፡ ዐቢይ ጾም መባሉም የጌታ ጾም ስለሆነ፣ ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች (አርእስተ ኃጣውእ) ድል የተነሱበት፣ ድል የሚነሱበት ስለሆነ ነው፤ በሕዝቡም ዘንድ ሁዳዴ ይባላል፡፡ ሁዳድ ማለት የመንግሥት መሬት የመንግሥት ርስት ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ሁዳድ በሚታረስበት ጊዜ፣ አዝመራው በሚሰበሰብበት ጊዜ ልጅ አዋቂ ሳይባል የመንግሥቱ ዜጋ ሁሉ ለሥራ ታጥቆ እንደሚነሣ፤ ይህንም የጌታን ጾም የጌታን ሁዳድ የክርስቶስ ዜጎች የሆኑ ምእመናን ሁሉ ይጾሙታል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንን መዝሙር ንባቡን ከዜማው አስማምቶና አጠናቅሮ የተናገረው ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው በሁዳዴ ለሚገኙት እሑዶች ሁሉ የተለየ መዝሙር ስለሠራላቸው እያንዳንዱ እሑድ በመዝሙሩ ስም ይጠራል፡፡
1. የመጀመሪያው እሑድ፡- ዘወረደ ይባላል፡፡ በመጽሐፉ መጀመሪያ አምላክ ከሰማይ መውረዱን፣ ሰው መሆኑንና መስቀሉን ስለሚያወሳ ነው፡፡ ሙሴኒም ይሉታል፡፡ ምናልባት ስለሙሴ ሕግና ጾመ ሙሴን ስለሚያነሣ ይሆናል፡፡
2. የሁለተኛው እሑድ፡- ቅድስት ይባላል፡፡ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ይሆናል፡፡
3. የሦስተኛው እሑድ፡- ምኲራብ ይባላል፡፡ በዚህ ሰንበት ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ በምኲራብ ገብቶ ማስተማሩ ይነገራል፡፡
4. ዐራተኛው እሑድ፡- መፃጉዕ ነው፡፡ ድውያንን መፈወሱን፣ ዕውራንን ማብራቱን፣ የሚያነሣ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡
5. አምስተኛው እሑድ፡- ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሁኖ ያስተማረው የዳግም ምጽአትን ነገር የሚያስታውስ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡
6. ስድስተኛው እሑድ፡- ገብርኄር ይባላል፡፡ የጌታውን ብር ተቀብሎ ያተረፈበት፣ በጌታውም ፊት ምስጋናን ያገኘው ሰው ታሪክ ይዘመርበታል፡፡
7. ሰባተኛው እሑድ፡- ኒቆዲሞስ ነው፡፡ በሌሊት ወደ ጌታ እየመጣ ይማር የነበረውን የኒቆዲሞስን ታሪክ የሚያስታውስ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡
8. ስምንተኛው እሑድ፡- ሆሣዕና ነው፡፡ ጌታ በአሕያ ውርንጭላ ሆኖ ሆሣዕና በአርያም እየተባለ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡ ከሠርከ ሆሣዕና እስከ ትንሣኤ ያለው ሰባት ቀን ሕማማት ይባላል፡፡ በእነዚህ ቀኖች ውስጥ ብዙ አዝማደ መባልዕት አይበሉም፡፡ ስግደት ይሰገዳል፡፡ የጌታን መከራና ሞት የሚያስታውሱ ምንባባት፣ ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከድርሳናት ተወጣጥተው በግብረ ሕማማት ይነበባሉ፡፡ አዳም ከፈጣሪው ተጣልቶ የኖረውን የጨለማና የመከራ ዘመን በማስታወስ መንበረ ታቦቱ በጥቁር ልብስ ይሸፈናል፡፡ ልብሰ ተክህኖውም ጥቋቁር ነው፡፡
ሐሙስ፡- ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ ጌታ በፍጹም ትሕትና የደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበበትና ከእነርሱም ጋር ግብር ያገባበት ምሥጢረ ቊርባንን ያሳየበት ዕለት ነው፡፡ "ፈረንጆች" ዕለቱን "Monday፣ Thursday ወይም " the last supper" ይሉታል፡፡ በዚህ ዕለት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐት የግብረ ሕማማቱ መጽሐፍ እንደሚያዘው ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ ከቅዳሴው ቀደም ብሎ ቄሱ ውሀውን በብርት አድርጎ በጌታ አምሳል የምእመናንን እግር ያጥባል፡፡ ጸሎተ ቅዳሴው ከተፈጸመ በኋላ ምእመናኑ ወደየቤታቸው ሂደው ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዳቦና ጒልባን ይበላሉ፡፡ ለትንሣኤ የተዘጋጀውም ጠላ የሚቀመሰውም የዚያ ዕለት ነው፡፡ ስለ ሕፅበተ እግር ካነሣን ዘንድ በሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያናት የሚታጠቡት በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አምሳል አሥራ ሁለት ሰዎች ናቸው፡፡ በእኛ ግን በቤተ ክርስቲያናት ያሉ ሁሉ ሴትም ሆነ ወንድ ይታጠባሉ፡፡ ነገር ግን አሠራራችን ምሳሌ ስለሚያጥረው እኛም እንደነርሱ አሥራ ሁለት ሰዎችን ብናጥብ የሐዋርያት ምሳሌ ነው፡፡
ከጸሎተ ሐሙስ በበነጋው ዓርብ የስቅለቱ መታሰቢያ ዕለት አጎበር ተሠርቶ ለስቅለቱ ነክ የሆኑ ምንባባት ሲነበቡ ይዋላል፡፡ ስግደቱም ከሰሞኑ ሁሉ የበለጠ ነው፡፡ ሠርክ ሲሆን እያንዳንዱ ምእመን ወደ ቄሱ እየቀረበ በሰሙነ ሕማማት ውስጥ የሠራውን ኀጢአት ይናዘዛል፡፡ ቄሱም በወይራ ቅጠል እየጠበጠበ ተጨማሪ ስግደት ይሰጣል፡፡ በአሥራ ሁለት ሰዓት ሠርሖተ ሕዝብ ይሆናል፡፡ ሁለት ቀን የሚያከፍሉ እህል ውሃ ሳይቀምሱ ያድራሉ፡፡ የማያከፍሉ ግን ከሐሙስ የተረፈውን ጉልባንና ዳቦ ይላክኩታል፡፡
"ቅዳሜ ጠዋት ምእመናኑና ካህናቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ› ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ፡፡ ሰላምን ፈጠረ፡፡ የምሥራች እየተባለ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበ ሁሉ ቄጠማ ይሰጣል፡፡ የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ምእመናኑም እየሰነጠቁ በራሳቸው ያስሩታል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላልመጡትም ካህናት በየበኩላቸው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ መስቀልና ቃጭል ይዘው፣ ቄጠማውን የምሥራች እያሉ ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም ገንዘብ ያለው፣ ገንዘብ ይሰጣል፡፡ ገንዘብ የሌለው ደግሞ ለጧፍ የሚሆን "ማግ" ልቃቂት ይሰጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከማዕዶት እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉትን ዕለታት ተከፋፍለው ይዘው ለሰበካቸው ካህናት ምግብ እያዘጋጁ ያመጣሉ፡፡ በጐንደርና በላስታ ሁሉም በአንድ ላይ በደጀ ሰላም ይመገባሉ፡፡ ወይንም ምእመኑ ካህናቱን በቤቱ ይጋብዛል፡፡ በአዲስ አበባና በሸዋ ግን ወደየንስሐ አባታቸው ቤት ምግብ እያዘጋጁ ይወስዳሉ፡፡ የአክፋይ ይሉታል፡፡ በዚያ ግን ገብረ ሰላመ ነው የሚባለው፡፡ ይህች ቅዳሜ፡- "ሰንበት ዓባይ" ትባላለች የፊተኛዪቱ ቅዳሜ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ ከሥራው ያረፈባት ዕለት እንደሆነች፣ ይህች ደግሞ የሦስት ዓመት ከሦስት ወር የማዳን ሥራውን በመስቀል ላይ ፈጽሞ በከርሠ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት ናት፡፡ ሁለተኛም ይህች ዕለት ‹ስዑር ቅዳሜ› ትባላለች፡፡ ስዑር መባሏም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም ነው፡፡ በባላገር ግን ‹ስዑር› ያለውን ይዘው ሰሞኑን ምንም ሳይሠሩ ሰንብተው በዚህ ዕለት ይሠራሉ፡፡ "ቅዳሜ ሹር" እንዲሉ ቄጠማው የምሥራች ምልክት መሆኑ ከታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ዓለም በንፍር ውሃ በተጥለቀለቀ ጊዜ፣ የኖ መርከብ ማረፊያ አጥታ ስትንሳፈፍ የውሃውን ሁኔታ ለመረዳት ኖ ርግብን በመርከቡ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፡፡ እርስዋም ቄማጠ ባፏ ይዛለት ትመለሳለች፡፡ ኖ በዚህ ቄጠማ የውሃውን መድረቅ ተረድቶ ተደሰተ፡፡ መርከቡንም ለማሳረፍ ተዘጋጀ፡፡ ቄጠማ ለጥፋት ውሃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ፣ አሁንም በክርስቶስ ሞት ማየ ሥራዌ፣ ማየ ድምሳሴ ኀጢአት፣ ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ፣ የምሥራች ሲባባሉ ምእመናን ቄጠማ ይዘው፣ ቄጠማ አስረው ይታያሉ፡፡ በዚህች ዕለት በአንዳንድ ቦታ ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ በአንዳንድ ቦታ አይቀደስም፡፡ የሚቀድሱት የሚሰጡት መልስ ካሣ የተፈጸመው ዓርብ ነው፡፡ ቅዳሴ መኖሩን የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጻፈው የዕለቱ "ክብር ይእቲ" ለማወቅ ይቻላል ይላሉ፡፡ አይቀደስም የሚሉት ደግሞ ምንም እንኳ የምንቀበለው ሥጋ፣ ነፍስ የተለየው፣ መለኮት የተዋሐደው ቢሆንም በትንሣኤ ድል ማድረጉን ከማየታችን በፊት መሥዋዕት አንሠዋም፡፡ ያሬድ የሠራው "ክብር ይእቲ" ቀድሱ የሚል ትእዛዝ የለውም ቅኔ ነው ይላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በቅዳም ስዑር ቅዳሴ እንዳይቀደስ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖአል፡፡




