የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤክርስቲያን ታሪክ

ክፍል 1

ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ

"ነገሥተ ሳባ ወዐረብ ጋዳ ያመጽኡ"

"የሳባና የዐረብ ነገሥታት እጅ መንሻ ያቀርባሉ" /መዝ.71,10/

ነቢዩ ዳዊት "ይገንዩ ቅድሜሁ ኢትዮጵያ ወጸላእቱሂ ሐመደ ይቀምሑ፤ ነገሥተ ተርሲስ ወደስያት አምኃ ያበውኡ፤ ነገሥተ ሳባ ወዐረብ ጋዳ ያመጽኡ፤ ወይሰግዱ ሎቱ ኲሎሙ ነገሥተ ምድር ኢትዮጵያውያን በፊቱ ይሰግዳሉ፤ ጠላቶቹም ዐመድ ይቅማሉ፤ የጠርሲስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታ ያመጣሉ፤ የሳባና የዐረብ ነገሥታትም እጅ መንሻ ያቀርባሉ፤ ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል" ብሎ /መዝ.71 9-10/በተናገረው ትንቢት መሠረት ሄሮድስ በነገሠበት ዘመን የይሁዳ ክፍል በምትሆን በቤተልሔም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ጥበበኞች ሰዎች ከምሥራቅ መጡ ----" ወደ ቤት ገብተው ሕጻኑን ከእናቱ ጋር አይተው ከፈረስ ከሠረገላ ወርደው ሰገዱለት፤ ሳጥናቸውን ከፍተው ኮረጁዋቸውን ፈትተው ወርቁን ዕጣኑንና ከርቤውን ግብር አገቡለት" /ማቴ.2 1-11/ ብሎ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ እንደጻፈው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ተወልዶ ሳለ ወርቅ ዕጣን ከርቤ ከገበሩለት ሦስት ነገሥታት አንዱ የኢትዮጵያ ንጉሥ ባዜን እንደነበረ ይተረካል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ "የግመሎች ብዛት፣ የምድያምና የጌፌር ግመሎች ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፤ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ፤ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ" /ኢሳ.60.6/ ብሎ በትንቢት እንደተናገረው የወርቅ እጅ መንሻ ያቀረበው ኢትዮጵያዊው ንጉሥ እንደነበር ይነገራል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ክርስቶስን ያወቀችውና መባ በማቅረብ ልደቱን ያከበረችው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቀዳማዊት ቤተ ክርስቲያን መባሉዋ በትክክል ነው፡፡

ከ1ኛ - 4ኛ ክፍለ ዘመን

"ነዋ ማይ ወመኑ ይከልአኒ ተጠምቆ "

"እነሆ ውሃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ማን ነው" /የሐ.ሥ.8፣36/

የጌታም መልአክ ፊልጶስን ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደሆነ መንገድ ሂድ አለው፤ ተነሥቶም ሔደ፤ እነሆም "ህንደኬ" የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘቡዋም ሁሉ የሰለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፤ መንፈስም ፊልጶስን ወደዚህ ሠረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው፤ ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና "በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?" አለው፤ እርሱም "የተረጐመልኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?" አለው፤ ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው፤ ያነብበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፡- እንደ በግ ወደመታረድ ተነዳ፣ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም፤ በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል" ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ እባክህ ነቢዩ ይህን ስለማን ይናገራል ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለሌላ አለው፤ ፊልጶስም መናገር ጀመረ፤ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ በመንገድም ሲሔዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም እነሆ ውሀ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድነው?" አለው፡፡ ፊልጶስም "በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዶአል" አለው፤ መልሶም "ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ" አለ፡፡ ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፤ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውሀ ወረዱ፤ አጠመቀውም፤ ከውሀውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፤ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና" /የሐ.ሥ.8፡26-39/ በማለት ወንጌላዊው ሉቃስ እንደተረከው የክርስትና እምነትና ጥምቀት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ34 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ንግሥት በሕንደኬ ጃንደረባ በባኮስ አማካይነት ነው፡፡ ያጠመቀውም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወንጌላዊው ፊልጶስ ነው፤ "ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምናለሁ" የሚለውን የእምነት ፎርሙላ በመናገር የጀመረና ለዓለም ያበረከተ ኢትዮጵያዊው ባኮስ ነው፡፡ አይሁድና ተንባለት እስከ ዛሬ ድረስ "ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ" መሆኑን ለማመን አቅቶዋቸው የተቸገሩበትንና ዓለምን የሚያስቸግሩበትን ክህደትና ኑፋቄ ሳይከተል "ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አውቆና አምኖ በማሳመን ለወገኖቹ ትክክለኛውን እምነት ስለ ሰበከ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እስከዛሬ ድረስ "ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ታምናለች፣ ትሰብካለች፤ ታሳምናለች፡፡ በዘመነ ሐዋርያት የክርስትና እምነትን በመቀበል የመጀመሪያው የወንጌል አዝመራ የሆነው ባኮስ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የእምነትና ሥርዐተ አምልኮ ሕንፃ የመሠረት ድንጋይ ነው፡፡ ለሐዲስ ኪዳን ኢትዮጵያም ዓለም ዐቀፍ እውቅና ያገኘ የቤተ ክርስቲያናችን መሥራች ነው፡፡ ባኮስ በዚህ ሃይማኖታዊ ጒዞው የሕገ ኦሪትንና የሕገ ወንጌልን ጽድቅ በአንድ ጒዞ በመፈጸም የራሱንና የአገሩን ስም በቅዱስ መጽሐፍ ለማስጠራት በቅቱአል፡፡

ክፍል ሁለት