የአጽዋማት ሥርዐት

ክፍል ሁለት

ባኮስ ወደ አገሩ ተመልሶ ከቅዱስ ፊልጶስ ስለ ክርስቶስ የሰማውንና የተረዳውን ለወገኖቹ ኢትዮጵያውያን እንደ አስተማረ የጥንት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሓፊ አውሳብዮስ ዘቂሣርያ ጽፎአል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችውም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ፊልጶስ የክርስትና አባቷ ስለሆነ በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንፃ ጽላት ቀርፃ ታከብረዋለች፡፡ በጸሎቱና በአማላጅነቱም ትታመናለች፤ ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ቅዱስ ማቴዎስ፣ ቅዱስ ናትናኤል፣ ቅዱስ በርተሎሜዎስ፣ ቅዱስ ቶማስ በኑብያና በኢትዮጵያ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ወንጌልን እንደ ሰበኩ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች እነሩፊኖስና እነ ሶቅራጥስ መስክረዋል፡፡

በ4ኛው መቶ ዓመት "ቅዱስና ያለ ተንኰል የሚኖር ነውርም የሌለበት ከኀጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል" /ዕብ.7፣26/ ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ሊቀ ካህናትነት እንደተናገረው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሾማቸው ከሐዋርያት ሐረገ ክህነት ተያይዞ የመጣ የሐዋርያት ተከታይ የሆነ ሊቀ ካህናት ማግኘት ይገባኛል ብላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲያስመጣላት ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማን ወደ እስክንድርያ ላከች፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ የእስክንድርያ ፓትርያርክም ራሱኑ ሾሞ ላከው፡፡

ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለችው በመጀመሪያው ምዕት ዓመት ይሁን እንጂ በሲኖዶስ ሕግ የኤጲስ ቆጶስ መንበር የተሰጣት በአራተኛው ምዕት ዓመት በ330 ዓ.ም. ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ተልኮ ሔዶ ከእስክንድርያው ፓትርያርክ ከቅዱስ አትናቴዎስ ዘንድ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሾሞ በመጣው በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መምህርነት በአብርሃና በአጽብሐ ዘመነ መንግሥት ጊዜ የክርስትና ሃይማኖት በዐዋጅ ተሰብኩዋል፡፡

ቅዱስ አባ ሰላማ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መንበረ ጵጵስናውን አክሱም ላይ አድርጎ በሀገራችን የወንጌልን ብርሃን በሰፊው ስለገለጠ ከሣቴ ብርሃን ተባለ፡፡

በዚሁ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የታወቀች ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ለመሆን መብቃቷን ታሪክ ያስረዳል፡፡

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ በምልዓት መፈጸም ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ ግዛት በሙሉ የወንጌልን ትምህርት ለማዳረስ የሚረዱት ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመ፡፡ ይልቁንም በዚያ ጊዜ ሊቀ ካህናት የነበረውን አንበረምን ሕዝበ ቀድስ ብሎ ኤጲስ ቆጶስነት ሾመው በሕዝበ ቀድስም ስብከት የኖባና የሳባ፣ የናግራንና የትግራይ፣ የአማራና የአንጎት፣ የቀጣ፣ የዘበግዱር ሕዝብ በክርስቶስ አምነውና ተጠምቀው ክርስቲያኖች ሆኑ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሱርስት፣ ከዕብራይስጥና ከፅርዕ ወደ ግዕዝ ቋንቋ መለሰ፡፡ የሳባውያንን የፊደል አቀማመጥ የለወጠውና አዲሱንም ከግራ ወደቀኝ የመጻፍና የማንበብ ዘዴ የፈጠረ እሱ ነው፡፡ ይልቁንም ድምፁን በመከተል 6ቱን የፊደል ድምፆች የጨመረ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን እንደሆነ ታሪክ ይናገራል፡፡

ከቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ሢመተ ጵጵስና ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ደረጃ ታወቀች፡፡

ከዚያም ጊዜ አንሥቶ እስከ 20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ከግብጻውያን ብቻ ጳጳሳት እየተሾሙ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ቈይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያውያን መካከል ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጳጳስ፣ አቡነ ፊልጶስ ኤጲስ ቆጶስ ሆነው እንደተሾሙ ታሪክ ይናገራል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከጥንታዊት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሥርዐተ እምነት አንድነትና የእህትማማችነት ህብረት ስለነበራት ግብፃውያን ጳጳሳት ሥልጣነ ክህነት በመስጠት ብቻ ተወስነው የቀረው የአስተዳደሩና የውስጥ አመራሩ ይዞታ ግን በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይካሄድ እንደነበር ታሪክ የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ፣ በሥርዐተ ትምህርትና በባህል ራሱን የቻለ አቋም የነበራትና ያላት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

ክፍል አንድ.......በቅርቡ ክፍል ሦስት