የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ጸዋትወ ዜማ

ክፍል አንድ

የዜማ አጀማመር

ዜማ ማለት ጣዕም፣ ለዛና ስልት ባለው ተከታታይ ቅንቀና የሚያሰሙት ድምፅ ማለት ነው፤ ወይም በልዩ ልዩ ሥነ ድምፅ ተቀነባብሮ፣ ተደራጅቶና ተስማምቶ ልዩ ስሜትና ተመስጦ ሊሰጥ በሚችል መልኩ የሚያሰሙት ቅንቀና ነው፡፡ ዜማ የተጀመረው በጥንተ ፍጥረት በመላእክት አንደበት ነው፤ መላእክት እንደተፈጠሩ ወዲያውኑ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን በጣዕመ ዜማ አመስግነዋል ኢዮ.38፣6፤ ከመጀመሪያው ጀምሮ እግዚአብሔር ሰውንና መላእክትን መፍጠሩ ስሙን አመስግነው ክብሩን እንዲወርሱ ነውና በጣዕመ ዜማ ማመስገንን በባሕርያቸው ውስጥ እንደ አንድ መሠረታዊ ፍላጎት አድርጎ ፈጥሮላቸዋል፤ ከዚህም የተነሣ ዜማን የመውደድ ዝንባሌ ተፈጥሮአዊ ሆኖ ይገኛል፤ ዜማን የመውደድ ዝንባሌ በመላእክትና በሰዎች ይበልጥ ጐልቶ ይታይ እንጂ ሕይወት ባላቸው በሌሎች ፍጡራንም በብዛት የሚታይ ነው፤ ለምሳሌ "አዕዋፍ ዘሠናይ ዜማሆሙ" ተብሎ የተመሰከረለትን የአዕዋፍ ዜማ መጥቀስ ይቻላል፤ እንግዲህ ይህንን ሁሉ ስንመለከት የስጦታ ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር ፍጡራንን በባሕርያቸው በዜማ የማመስገን ፍላጎትና ዝንባሌ እንዲኖራቸው አድርጎ በመፍጠሩ የዜማ መገኛውና ምንጩ እርሱ ራሱ ሆኖ እናገኘዋለን፤ ከጥንተ ፍጥረት ጀምሮ በጣዕመ ዜማ ማመስገን በሰማያውያን ፍጡራን ዘንድ የማያቋርጥ መደበኛ ሥራ ነው፤ ራእ.4፣9፣ ኢሳ.6፣2-4፡፡ እንደዚሁም ዜማ በተፈጥሮ የተገኘ ተወዳጅ ስጦታ እንደመሆኑ መጠን ሁሌም የመንፈስ ምግብ ነውና ሰዎች ከጥንተ ፍጥረት ጀምሮ ሲጠቀሙበት ኖሮዋል፤ ዘፍ.4፣21፤ ከዚህም የተነሣ ጣዕሙ፣ ይዘቱና ስልቱ ይለያይ እንደሆነ ነው እንጂ ሰዎች ከተፈጠሩበት ጊዜ አንሥቶ ከጣዕመ ዜማ የተለዩበት ጊዜ የለም፤ በመሆኑም በየትኛውም ክፍለ ዓለም የሚገኝ ሕዝብ የራሱ የሆነ ዜማ አለው፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ ዜማ በአምስት ዓይነት ተከፍሎ ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል፤ እነዚህም፡-

ሀ. እግዚአብሔር የሚመሰገንበት መንፈሳዊ ዜማ /ማህሌት/

ለ. ሕዝብ በደስታ ጊዜ የሚጠቀምበት የደስታ ዜማ /ዘፈን/

ሐ. ሕዝብ በኀዘን ጊዜ የሚጠቀምበት የኀዘን ዜማ /ልቅሶ/

መ. ነዳያን በችግር ጊዜ የሚለምኑበት የልመና ዜማ /ልመና/

ሠ. በሰልፍ ጊዜ ለመቀስቀሻ የሚጠቀሙበት የፉከራ ዜማ /ቀረርቶ/ ናቸው፡፡

ዜማ ለእነዚህ ሁሉ የጋራ መጠርያቸው ነው፤ ሆኖም የዜማዎቹ ድምፀ ቃና፣ ሥነ ቃልና እንቅስቃሴ የአንዱ ከሌላው የተለያዩ ናቸው፡፡ እንግዲህ ስለ ዜማ አጀማመርና አመጣጥ በአጭሩ ይህን ያህል ካልን በኋላ የዚህ ጽሑፍ ዋና ርእስ ወደሆነው "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ጸዋትወ ዜማ" ወደሚለው ዝርዝር ገለጻ እንገባለን፡፡

ክፍል ሁለት