የአጽዋማት ሥርዐት

ክፍል ሁለት

1. ቅድመ ክርስትና የነበረ ዜማ

የኢትዮጵያ ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ከአምልኮተ እግዚአብሔር የተለዩበት ጊዜ የለም፤ በመሆኑም ዜማ ተፈጥሮአዊ ስጦታ እንደመሆኑ መጠን በተፈጥሮ ያገኙትና የራሳቸው የሆነ የእግዚአብሔር ማመስገኛ ጣዕመ ዜማ አልነበራቸውም ማለት አይቻልም፡፡

ኦሪት ገና ወደኢትየጵያ ከመግባቱ በፊት ስብሐተ እግዚአብሔር፣ አምልኮተ እግዚአብሔርና ፈሪሀሃ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ እንደነበረ ይታወቃል፤ አምልኮት ካለ ምስጋና አለ፤ ምስጋናም ካለ ዜማም አብሮ አለ፤ ከዚህ ሁኔታ ስንመለከት ከሕገ ኦሪት መምጣት በፊት በኢትዮጵያ በዜማ ማመስገን ነበረ ማለት ይቻላል፡፡

ከዚህም በኋላ በኢትዮጵያ ዘመነ አበው አልፎ ዘመነ ኦሪት ሲተካና በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን ታቦተ ጽዮንና ሌዋውያን ሲመጡ የመዝሙራት መጻሕፍት አብረው ስለመጡ የዜማው መልክ በመሣርያ፣ በዓይነትና በአጠቃቀም ተጨማሪ መልክ መያዙ አልቀረም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ /መዝ.150፣1-5፣ ዜና መዋ.ቀዳ.15፣16፤ 16፣4-37/ እንደሚያስረዳው በዳዊትና በሰሎሞን ጊዜ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በከበሮ፣ በጸናጽል፣ በመሰንቆ፣ በበገና፣ በዕንዚራ፣ በቀንደ መለከት፣ በዕልልታና በሆታ እግዚአብሔር በዜማ ይመሰገን እንደነበረ ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ ምስጋናና የምስጋና መሣርያ በዋነኛነት ይጠቀሙ የነበሩ የታቦተ ጽዮን አገልጋዮች የነበሩ ሌዋውያን ካህናት መሆናቸውንም መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል /ዕዝ.3፡10/፡፡

በቀዳማዊ ምኒልክ አማካኝነት ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ሌዋውያንም አብረው ስለመጡ ዜማቸው፤ ማሌታቸውና የማሌት መሣርያቸው ሁሉ በዚያን ጊዜ አብሮ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶአል፤ አገሪቱም ይህንን የዜማ ስልት ከነመሣርያው እስከ ዘመነ ክርስትና ስትገለገልበት ቈይታለች፤ የዚህ ዓይነቱ ጣዕመ ዜማ አገልጋዮችም ታቦተ ጽዮን በምትኖርበት ድንኳን ውስጥ ከዓመት እስከ ዓመት ያለማቋረጥ የሚያገለግሉ ስለነበሩ "ካህናተ ደብተራ" ይባላሉ፤ ትርጓሜውም ታቦተ ጽዮን በምትኖርበት ድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት ማለት ነው፤ ይህ ስም ከጥንት ጀምሮ የቈየ የመዓርግ ወይም የሙያ ስም ነው፤ ስያሜው እስከ ቅርብ ጊዜ ትልቅ የመዓርግ ስም ሆኖ ለቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይሰጥ ስለነበረ ሊቃውንቱ ደብተራ እገሌ እየተባሉ ይጠሩበት ነበር፡፡

እነዚህ በዘመነ ኦሪት የመጡ የዜማ መሣርያዎች፣ አለባበሶችና የመዝሙር አጠቃቀም ስልቶች እስከዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን ስትገለገልባቸው ትገኛለች፡፡ ለምሳሌ ከዜማ መሣርያዎች መካከል፡- ከበሮ፣ ጸናጽል፣ መለከት፣ መሰንቆ፣ በገና ወዘተ ይገኙበታል መዝ.150፣1-5፤

ከአለባበስም ረጅም ቀሚስ፣ ጥምጥም፣ መጐናጸፊያ /ጋቢ/ እና ካባ ወዘተ ይገኙባቸዋል ዘሌ.8፣7-9 ፡፡

ከመዝሙር ስልት ደግሞ የቅዱስ ያሬድ የምዕራፍ ዜማ ምዕዛል ስልት ይገኝበታል ዕዝ.3፣11፡፡

2. ዜማ በክርስትና ምሥረታ ጊዜ፡-

ኢትዮጵያ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመርያ አካባቢ የክርስትና ሃይማኖትን በብሔራዊ ደረጃ ስትቀበል ለምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ማስፈጸምያ የሚሆን ክርስቲያናዊ ዜማ ነበራት፤ ይህ ዜማ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እንደሚታየው ለአገልግሎት ማስፈጸሚያ ያህል በመጠኑ ያገለግል የነበረ ዜማ እንጂ እንደ አሁኑ ጥልቀት፣ ምጥቀትና ርቀት ያለው፣ የተደራጀና የተቀነባበረ ዜማ አልነበረም፤ ከ330 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አምስት መቶ ዐርባ ዓ.ም. በዚሁ ዜማ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሲሰጡ፣ እግዚአብሔርም ሲመሰገን ኖሮአል፤ ከአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ግን እግዚአብሔር ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ሰዎች በፊቱ ይሰግዳሉ /መዝ.71፣9/ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ታደርሳለች /መዝ.67፣31/ ሲል በዳዊት አንደበት የመሰከረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖትና አምልኮተ እግዚአብሔር በልዩ ጣዕመ ዜማ እንዲታጀብ በመፈለጉ ከአኲስም ጽዮን ካህናተ ደብተራ መካከል አንዱን ካህን ለታላቅ ሰማያዊ ጣዕመ ዜማ መገለጥ መረጠ "ቅዱስ ያሬድ"፡፡

ክፍል አንድ.......በቅርቡ ክፍል ሦስት