‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ››
‹ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን አደረገ› ኤፌ. 2፡14-15
መለያየት የኃጢአት ውጤት እንደሆነ ሁሉ፣ አንድነት ደግሞ የሰለም፣ የፍቅርና የስምምነት ውጤት ነው ፡፡
የሰው ልጅ በተከተለው የተሳሳተ አማራጭ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ኅብረት ወይም ግንኙነት ሲያጣ ከሌሎች ፍጠረታት ጋር የነበረውን አንድነትም በተመሳሳይ አጥቶአል፤ ይልቁንም የእርስ በርስ መግባባት በመጥፋቱ የሰው ዘር በተለያየ ጎራ እየተሠለፈ በጥላቻ መተያየቱ የዘወትር ክስተት ሆነ ፡፡
የተከሰተው መለያየት በሥጋዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሕይወትም ጭምር ነበር፤ ጌታችን፣ አምላካችን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ዓለማችን በመንፈሳዊ ሕይወቷ በሁለት ጎራ ተለይታ ትኖር ነበር፤ በአምልኮተ እግዚአብሔርና በአምለኮተ ጣዖት፡፡
እግዚአብሔርን ሲያመልኩ የነበሩ እሥራኤላውያን ሕዝበ እግዚአብሔር ተብለው ሲጠሩ፣ ጣዖትን ያመልኩ የነበሩትም ጣዖት አምላኪዎች ይባሉ ነበር፡፡
ሁለቱም ወገኖች የማይግባቡና በከፋ ጥላቻ ይኖሩ የነበሩ ናቸው፤ ቢሆንም ጥላቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውምና ይህን የሚያስወግድ የእግዚአብሔር ጥበብ በዓለም እንዲገለጥ የእግዚአብሔር አምላካዊ እቅድ ነበር፤ ይህም እቅድ በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጻሚ ሆነ፡፡
የሰው ጠላቶች ኃጢአትና እርሱን ተከትሎ የመጣው መለያየት ነው፤ የእግዚአብሔር ጥበባዊ አሠራርም ያነጣጠረው በኃጢአትና በውጤቶቹ ላይ ነው፡፡
በመሆኑም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ባፈሰሰው ደሙ ኃጢአትን፣ ጥላቻንና መለያየትን ገደለ፤ አስወገደ፤ የበሽታ አምጭ ሕዋሳት ሊጠፋ የግድ ነውና ኃጢአት ሲጠፋ መለያየቱም ቀረ ፡፡
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ መስቀል ሰዎች የሚድኑት ክርስቶስን በማመን በሚገኝ ጽድቅና እርሱን ተከትሎ በሚፈጸም ስነ ምግባር እንጂ እስራኤል በኦሪታቸው አሕዛብ በጣዖታዊና በባህላዊ እምነታቸው አለመሆኑን አረጋገጠ፡፡
በመስቀሉ የተገኘ ሰላምና ዕርቅ ሁለቱም ወገኖች የነበራቸውን ልዩነት በመተው ሁሉም በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲሰበሰቡ በማስቻሉ የመስቀሉ ውጤት ሰላም፣ ዕርቅና ስምምነት ሆነ፤ ከዚህም የተነሣ በመስቀሉ ጥልን ገደለ፣ ሁለቱንም ወገኖች አስታርቆ አንድ አደረገ፣ ሰላምንም አወጀ ተብሎ ተበሰረ ፡፡
የመስቀሉ ነገር ማለት የወንጌል ትምህርት ማለት ነው፤ የወንጌል ትምህርት ደግሞ እኩልነትን እንጂ መበላለጥን፣ አንድነትን እንጂ መለያየትን ሰላም፣ ፍቅር፣ ስምምነትን እንጂ ጥላቻን አያስተናግድም፤ ለዚህም ነው መስቀል ሰላማችን ነው በማለት ቅዱስ መጽሐፍ የሚያስተምረን ፡፡
የመስቀል ዕርቅ በእግዚአብሔር ዘንድ የተከናወነ መሠረታዊ እርቅ ነውና በሰዎችና በሰዎች መካከል የነበረውን ጥልና መለያየት ማስወገድ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ነው፤ ከላይ ከፍ ብሎ እንደተገለፀው ኃጢአት ሰውን የለየው ከብዙ ነገር ነው፤ ይኸውም፡-
-
- ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ልጅነት፤
-
- ፈጣሪው ከሰጠው ርስት ከመንግሥተ ሰማያት ወራሽነት፤
-
- ከፍጡራን በላይ ከነበረው ደረጃና
-
- ከማኅበረ መላእክት አንድነት ሁሉ ለይቶታል፡፡
ይሁንና ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ በፈጸመው የማስታረቅ ተግባር እነዚህ ሁሉ እንዲስተካከሉ በማድረግ በሰማይና በምድር ያሉትን ሁሉ አስታረቀ፡፡
ስለሆነም በመስቀል ላይ በከፈለው መሥዋዕትነትና ባፈሰሰው ደሙ በሰማይና በምድር የነበሩትን ሁሉ በማስታረቅ ሰላምን አደረገ ተብሎ የምሥራቹ ተነገረን፤ ሰው በኃጢአት ምክንያት ያጣውን ሁሉ በመስቀሉ ኃይል ማግኘትን ችሏል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!
የመስቀልን በዐል የምናከብርበት መሠረታዊው ምክንያት ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ተባብለን ለመለያየት ሳይሆን የመስቀሉ ነገር ያመጣልንን ሰላምና እርቅ በማስታወስ በፍቅርና በስምምነት አንድ ሆነን ማኅበራዊና መንፈሳዊ ኑሮአችንን ለማስተካከል ቃል በመግባትና እርሱን ለመተግበር መነሣሣት ሊሆን ይገባል ፡፡
ዓለማችን እግዚአብሔር በፈቀደላትና በሰጣት ዕውቀት ብዙ የአሠራር ዘዴዎችን አግኝታለች፤ ይሁን እንጂ የመስቀሉ ነገር ካስተማረው ከእርቅና ከሰላም በቀር ሌላ የልዩነት ማስወገጃ መሣሪያ ማስገኘት አልቻለችም፤ ልዩነቶችን ሊያጠቡ የሚችሉ የተለያዩ አባባሎችና ስልቶች አሉኝ ብላ ለማውራት ብትሞክርም ከመስቀሉ ትምህርት የተገኙና እነርሱን ከልሶ መናገር እንጂ ሌላ ሆኖ አይገኝም፡፡
በመከባበር፣ በመተማመንና በመደጋገፍ ላይ የተመሠረተ የሰዎች እኩልነትና አንድነት የሚያስገኘውን ጥቅም በተመለከተ ከዛሬዎቹ የዓለም አባባሎች በፊት የመስቀሉ ነገር አስቀድሞ ያወጃቸው ናቸው፤ ከዚህ አኳያ የመስቀሉ ነገር ከጥበብ ሁሉ በላይ መሆኑን በዚህ ማወቅና መገንዘብ እንችላለን፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!
ዛሬ በእግዚአብሔር ምሕረትና ይቅርታ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቀድሞ ጀምሮ በእግዚአብሔር ዘንድ የተመደበላትንና የተመሰከረላትን የሃይማኖትና የአንድነት ጉዞ ተከትላ ወደፊት እየገሰገሰች የምትገኝበት ጊዜ ነው ፡፡ ሕዝቦቻችን ቋንቋና ጥቃቅን ባህሎች ሳይነጣጥሉዋቸው ለጋራ ዕድገትና ብልጽግና ዳር እስከዳር በቅን መንፈስ ተነሣስተዋል ፡፡ የመስቀሉ ዓላማ ልዩነትን በማስወገድ አንድነትንና ሰላምን ማረጋገጥ ነው፤ ይህ የአንድነት ሰንሰለት እስከመቼም ቢሆን መበጠስ የሌለበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የልማትና የዕድገት ዋስትና አንድነታችን፣ የእኩልነትና የሰላም መርሆቻችን ናቸው ፡፡ ከጥንት ጀምሮ ሳይቋረጥ ከእኛ ዘንድ የደረሰውና በአሁኑም ጊዜ ተጠናክሮ በመስቀል የሚገኘው የአንድነት፣ የእኩልነትና የሰላም ጸጋችን ከመስቀሉ የወረስነው ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡
ስለሆነም አሁን የተያያዝነው ጉዞ ምንጩ የመስቀሉ ነገር መሆኑን በውል ተገንዝበን እንደ ዓይን ብሌን በመንከባከብ ሃይማኖታችንን፣ ልማታችንን፣ ሰላማችንን፣ አንድነታችንንና እኩልነታችንን ጠብቀን ወደ ፊት መቀጠል ይገባናል፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን፤
‹‹እግዚአብሔር አምላካችን ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ››
አሜን!
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ
የበዓሉን አከባበር በፎቶገራፍ ይመልከቱ!




