በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ

ሠላሳኛ መደበኛ ዓመታዊ ስብሰባ

ቃለ ጉባኤ

    አጠቃላይ ጉባኤው ከጥቅምት 7-11 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም. ተካሔዷል፡፡

  • • ጉባኤው በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ርእሰ መንበርነት፤
  •  

 

 

 

• በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የኢሉባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የስብሰባው መርሐ ግብር አስተባባሪነት የተካሔደ ሲሆን የጉባኤው አባላትም፣

  • • የመላ ኢትዮጵያ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት፣
  • • በውጭ ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳትና ተወካዮች፣
  • • ክቡራን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጆች፣
  • • የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪየውና ድርጅቶች ሓላፊዎች ፣
  • • የመላው አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣
  • • የመላው አህጉረ ስብከት የካህናት፤ የምእመናን፤ የስብከተ ወንጌል፣ የሰበካ ጉባኤ አደራጆችና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮች ናቸው፡፡
  • • እንዲሁም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየሥራ ዘርፉ ሠራተኞች በተመልካችነት ጉባኤውን ተሳትፈዋል፡፡

የጉባኤው አጠቃላይ ገጽታ

በወጣው መርሐ ግብር መሠረት ጉባኤው በቅዱስነታቸው ጸሎተ ቡራኬ ከተከፈተ በኋላ ጸሎተ ወንጌል ተደርሷል፡፡ በዚህ ጊዜም

  • "ስምዓነ አምላክነ ወመድኃኒነ" የሚለው መዝውረ ዳዊት ከተሰበከ በኋላ ከማቴዎስ ወንጌል በም.18 ከቁጥር 18 ጀምሮ ያለው በቅዱስነታቸው ተነቧል፡፡
  • በመቀጠልም በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ አማካይነት ስለጉባኤው መርሐ ግብር መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
  • ቅዱስነታቸው በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የመታሰቢያ ጸሎት እንዲደረግ ለጉባኤው አሳስበው ጸሎቱን ከመሩ በኋላ የመክፈቻ ቃለ ምዕዳንና መመሪያን ሰጥተዋል፡፡
  •  

    ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳንና መመሪያ

    "በሠላሳኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የመጣችሁ ሁላችሁ፡-

    የዘመናት ጌታ እግዚአብሔር አምላካችን ሁላችንንም በያለንበት ጠብቆ በሰላም ለመገናኘት ስለአበቃን እናመሰግነዋለን፡፡ እንኳን በሰላም መጣችሁ፤ እኛ የቤተ ክርስቲያኒቱን መመሪያ ለመቀበል ለመፈጸምና ለማስፈጸም በየደረጃው እዚህ የምንገኝ ሓላፊዎች የሓላፊነት ግዴታችንን ለመወጣት ቃል የገባንበት ዐላማ ስለሆነ የዚህን ተልእኮ ለማሳካት ያላሠለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

    በምንሰጠው ማኅበራዊ አገልግሎት ሁሉ ሰዎች በመንፈሳዊውና በሥጋዊው ሕይወታቸው ችግር እንዳይደረሰባቸው የማድረግ ተልእኮ ከየአንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡ በዓለማችን እኸል እያለ በምግብ እጦት፣ ውሃ እያለ በውሃ እጦት የሚቸገሩ፣ ልብስ እያለ የሚታረዙ እንዳሉ ይሰማል፡፡ ይህን ችግር ለማቃለል ያለው ለሌለው እንዲያካፍል የማስተማር፣ የማስተባበር ሓላፊነትና ዐደራ ተጥሎብናል፡፡ ይህም ሓላፊነት በሐዋርያው በቅዱስ ጴጥሮስ አማካይነት "በጎቼን ጠብቁ ጠቦቶቼን አሰማሩ" ተብሎ የተሰጠ ዐደራ ነው፡፡

    በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች ልጆቻችን ተጠቃለው ወደ ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት እየመጡ ያለበት ጊዜ ስለሆነ እነርሱን የማስተባበር፤ የማስተማርና የመቆጣጠር፣ ለሓላፊነት ደረጃም እንዲበቁ ማድረግ ታላቁ ሥራችን ነው፡፡ ርዳታን ማድረግ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ አውቀዋለሁ፤ አውቃታለሁ የሚል ሚዛኑን ያልጠበቀ አመለካከት ሳይኖር፤ ሁሉንም በእኩልነት ዐይን በመመልከት ማገልገል ያስፈልጋል፤ ይህን ሁሉ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ደግሞ ሰላም፣ ግልጽነት፣ተጠያቂነትና ተባብሮ መሥራት ግዴታችን ይሆናል፣፣ እግዚአብሔር የማይወደው ነገር ቢኖር "እኔ እበልጣለሁ፤ እኔ ብቻ አውቃለሁ" ባይነትን ነው፡፡

    ስለዚህ ይህ ሠላሳኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ባለፉት ሃያ ዘጠኝ ጉባኤያት የተላለፉ ውሳኔዎችንና የተገኙ ውጤቶችን ገምግመን የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ተግቶ ለመሥራት የምንወያይበትና የምንዘጋጅበት ዐቢይ ጉባኤ ስለሆነ በመርሐ ግብሩ በቀረቡት ዐበይት የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ ተወያይተን ለሰመረ ውጤት እንድንበቃ የሐዋርያትን፣ የሊቃውንትን ጉባኤ የመራ እግዚአብሔር አምላካችን የእኛንም ጉባኤ በመምራትና በመባረክ በሰላም እንዲያስፈጽመን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን" በማለት ቅዱስነታቸው ሰፋ ያለ ቃለ ምዕዳንና መመሪያን ሰጥተዋል፡፡

    ከቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና መመሪያ ቀጥሎም ለጉባኤው ሒደት በወጣው መርሐ-ግብር መሠረት በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠ/ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የኢሉባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በክቡር ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሐ የጠ/ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የመላዋ ቤተ ክርስቲያናችን የ2ዐዐ3 በጀት ዓመት የሥራ ክንውን አጠቃላይ ሪፖርት ቀርቦ ጉባኤው በጥሙና ተከታትሎታል፡፡

    መርሐ ግብሩ በቅዱስነታቸው ርእሰ መንበርነት፣ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አስተናባሪነት እየተመራ በየዕለቱ ቀጥሎ የየሀገረ ስብከቱ ዓመታዊ ዘገባዎች በቅደም ተከተል ተሰምተዋል፡፡

    እንዲሁም በውጭ ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳትና ተወካዮች የየበኩላቸውን ሪፖርት ከያዙት ፍሬ በረከት ጋር አቅርበው ጉባኤው በአክብሮት ሰምቶታል፡፡ በመቀጠልም የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ፣ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ሪፖርት በየሐላፊዎቻቸው በቅደም ተከተል ቀርቦ ጉባኤው አድምጧል፡፡

    ከዚያም የጐደለውን ለማሟላት ፣ የጠመመውን ለማቃናት፣ ለችግሮች ሁሉ መፍትሔን ለማስገኘት፣ ዕቅዶችንም ለማሳካት የጥያቄና መልስ ፕሮግራም ተካሔዶ ሰፊ ውይይት ተደርጐበታል፡፡ ከዚህም አንጻር ተገቢው ማብራሪያ እየተሰጠ ጉባኤው በፍጹም መደማመጥ አትኩሮትና ትጋት በተመላው ታላቅ ትዕግሥት ተከናውኗል፡፡

    ከላይ እንደተገለጸው ይህ ዓመታዊ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ እድገትና ልማት አለኝታ የሆነው ዐቢይ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፡-

    • በብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ፣ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ርእሰ መንበርነት ሰላምና ጸጥታ በተመላው ሁኔታ ተመርቷል፡፡
    • በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የኢሉባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለጉባኤው እዝነ ልቡና በማይከብድ እጅግ የለዘበ አባታዊ አገላለጽ በደስታ ተስተናብሯል፡፡
    • ጉባኤው በየመሐሉ በቀረቡት ያሬዳዊ ጣዕመ ዜማም ሙቀተ መንፈስ ቅዱስን እያገኘ ልቡናውን በማለምለም ብሩህ አእምሮን አሥርጿል፡፡
    • ይህ ታሪካዊ እና ብሔራዊ ጉባኤ ከሃይማኖቱ የተነሣ በረድኤተ እግዚአብሔር እየታገዘ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ ከተላለፈ በኋላ ለ2ዐዐ4 የበጀት ዓመት ከላይ እስከ ታች በመላዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሥራ መመሪያ ይሆን ዘንድ የሚከተለውን የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ የጋራ አቋም መግለጫም በተባበረ ድምፅ አውጥቷል፡፡

    የውሳኔ ሐሳብና የጋራ አቋም መግለጫ፡-

    1. ሠላሳኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ በቅዱስነታቸው ጸሎተ ቡራኬ ከተከፈተ በኋላ ቅዱስነታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተናዊ ገጽታ የሚዳስስ መመሪያ ትምህርትና ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና ምክትል ሥራ አስኪያጁ የዘመኑን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴና የወደፊቱን ዕቅድ የሚያሳይ ሪፖርት ለምልአተ ጉባኤው አሰምተዋል፡፡

    ምልአተ ጉባኤው ከቅዱስነታቸው የተሰጠውን መመሪያና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር የቀረበውን ዓመታዊ ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ በሠነድነት ተቀብሎ በመሉ ድምፅ አጽድቆታል፡፡

    2. ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር በቀረበው አጠቃላይ ሪፖርት እንደተገለጸው ብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በክብር እየተገኙ ያለ ዕረፍት ያበረከቱትን መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ ያስተላለፉትን አባታዊ መመሪያ፣ ያደረጉትን ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ሁሉ ጉባኤው ከልብ በመነጨ ስሜት ተቀብሎታል፡፡

    በቀጣዩም የሥራ ዘመን፣ ጤንነታቸው ተጠብቆ ሌት ከቀን የሚያስቡላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ለበለጠ እድገት እንዲያበቋት በመመኘት ከፍተኛ የድጋፍ ሓሳባችንን እናቀርባለን፡፡

    3. በቅዱስነታቸው አባታዊ ርኅራኄና አመራር ሰጭነት፣ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥናት አቅራቢነትና አስፈጻሚነት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ወሳኝነት፣ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ ቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር ለሚገኙ ሠራተኞች በተደረገው የደመወዝ ማስተካከያ እጅግ ከብዶ የነበረውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም አስችሏል፡፡

    ስለዚህ ይህ ታሪካዊና የተቀደሰ ተግባር የሠራተኛውን ሞራል የገነባ፣ ለሥራም የአበረታታ፣ የመላ ቤተሰቡንም ሕይወት የለወጠ በመሆኑ ጉባኤው ከፍ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

    4. በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉባኤ ሊቃውንት ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት እየተመረመሩ መታተማቸው በሪፖርቱ ተገልጾአል፡፡

    ለወደፊቱም በቤተ ክርስቲያናችን እየተዘጋጁ የሚታተሙ መጻሕፍትና መዝሙራት ሁሉ በጉባኤ ሊቃውንት እየተመረመሩ እንዲታተሙ ጉባኤው በአጽንዖት ያሳስባል፡፡

    5. ትምህርት ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አገልግሎት የሚያበቃ የዕውቀት ሁሉ ምንጭ ስለሆነ የአብነት ት/ቤቶች ትምህርት ከዘመናዊው ጋር ተቀናጅቶ ሊሰጥ በሚችልበት ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ሥርዐተ ትምህርት በትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ማእከልነት እንዲዘጋጅ ሆኖ ለአብነት ትምህርት ስለሚሰጠው ትኩረት በሰሜን ሺዋ፣ በለሚ ወረዳ በአንድ በጎ አድርጊ የተሠራውና በቅዱስነታቸው የተመረቀው፣ ጉባኤውንም ያስደሰተው ታላቅ ምሳሌ ስለሚሆን ለአብነት ት/ቤቶች መምህራንና ደቀ መዛሙርት የሚደረገው ድጋፍና ክብካቤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው ተስማምቷል፡፡

    ሦስቱ መንፈሳዊያን ኮሌጆቻችንም በመማር ማስተማሩ ዘርፍ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ፣በጀታቸውንም በልዩ ልዩ ገቢ ለመደጐም የአሳዩት ጥረት አበረታች ስለሆነ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሆኖ በሥነ ምግባር የታነጹ ደቀ መዛሙርትን ኩትኩተው እንዲያስመርቁ ብርቱ ትኩረት እንዲሰጡ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

    6. ስብከተ ወንጌል የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዐቢይ ተልእኮና የማይቋረጥ ልሳን በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡

    ስለዚህ ከመምሪያው ዕውቅና ውጭ በሆነ መንገድ በዘፈቀደ በስብከተ ወንጌል ስም በግለሰቦች የሚደረገው ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ እንዲገታ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በተሰጠው መመሪያ መሠረት የሚያደርገውን ክትትልና ቁጥጥር አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶችም የወላይታ ኮንታ ሀገረ ስብከትን መልካም አርአያ አድርገው ፈቃድ ለሌላቸው ሰባክያን ሁሉ መድረክ እንዳይሰጡ ጉባኤው አስገንዝቧል፡፡

    • ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያና ማጠናከሪያ አገልግሎት ይውል ዘንድ በመዋጣት ላይ የሚገኘው ከመቶ አንድ ክፍያ ጉዳይ በአብዛኞቹ አህጉረ ስብከት እንዳልተከፈለ ከቀረበው ሪፖርት መረዳት የተቻለ ስለሆነ በተዘረጋው ማዋቅር መሠረት በሁሉም አህጉረ ስብከት ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ ባሉ ሠራተኞች ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ገንዘቡም ለዐላማው በትክክል እንዲውል ይደረግ ዘንድ ጉባኤው በአጽንዖት ይጠይቃል፡፡

    7. መልካም አስተዳደር ለቅ/ቤተ ክርስቲያን ሥራ መቀላጠፍ፣ ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘት፣ ሥራን ዐቅዶ ለመምራት ፍትሐዊ ውሳኔን ለመስጠት፣ ገንዘብና ንብረትን ለመጠበቅና በተገቢው ሥራ ላይ ብቻ ለማዋል ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡

    በመሆኑም በአብዛኞቹ አህጉረ ስብከት ለአስተዳደራዊ ሥራ ብቃት ሥልጠና መሰጠቱ ስለተገለጸ የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅር በጠበቀ መልኩ ሥልጠናው እንዲቀጥል፣ ሕግና መመሪያም ተጠብቆ እንዲሠራ ክትትልና ብርቱ ጥረት ይደረግ ዘንድ ጉባኤው ጥያቄውን ያቀርባል፡፡

    8. ሀ/ ሰበካ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያናችን ጠቅላላ አገልግሎት መፈጸማያና ማስፈጸማያ ዋናው ተቋማችን ሰለሆነ መምሪያው እንዲጠናከር አስፈላጊው ሁሉ እየተሟላለት ቢሆንም ከአለው ሓላፊነትና የሥራው ስፋት አንጻር የተጓደለ ቢኖር በበለጠ ተሟልቶለት ከበላይ አካል በሚሰጠው መመሪያ መሠረት የማደራጀትና ማጠናከር ሥራውን እንዲቀጥል፣

    ለ/ ከዚህም ጋር ከላይ እስከ ታች የገንዘብ አያያዝ፣ የንብረት አጠባበቅ የምእመናን ምዝገባና የቅጾች ተጠናቆ አሞላል፣ የፐርሰንት አወጣጥ በየደረጃው የቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ ተጠብቆ በጥንቃቄ እንዲሠራ፤

    ሐ/ የሰበካ ጉባኤ አባልነት አስተዋፅኦም በየዓመቱ እድገትን ያሳይ ዘንድ ከአጥቢያ

    ቤተ ክርስቲያን ካህናተና ልዩ ልዩ ሠራተኞተ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ ያሉት በያጥቢያቸው በሰበካ ጉባኤ እየተመዘገቡ አስተዋፅኦ በመክፈል ለምእመናን መልካም ምሳሌ እንዲሆኑ በመምሪያው በኩል ያልተቆጠበ ክትትልና የማስፈጸም ሥራ እንዲሠራ ጉባኤው አምኖበታል፡፡

    9. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አስተዳደርዋን የምትመራበት በርካታ መመሪያዎች እንዳሏት ይታወቃል፡፡ ከእነዚህም መካከል ቀደም ሲል ህልውናን አግኝቶ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት እየሰጠ ያለው ቃለ ዐዋዲ ነው፡፡ ይኸው ቃለ ዐዋዲ እስከ አሁን ድረስ ሲሠራበት የቆየና አሁንም እየተሠራበት ያለ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ አካባቢ የመንግሥት ዕውቅና የለውም የሚል ጥያቄ እያስነሣ መሆኑ ለጉባኤው ስለተገለጸ በሥራ ላይ ያለው ቃለ ዐዋዲ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሻሻልና ለመንግሥት ቀርቦ ዕውቅና እንዲያገኝ እንዲደረግ ጉባኤው በአትኩሮት ያሳስባል፡፡

    10. በዓላትን ማክበር በጥንተ ፍጥረት በልዑል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጠ የመልካም መንፈሳዊ ሥራና የዕረፍት ቀን እንደሆነ ይታመናል፡፡

    ስለዚህ የካህናት አስተዳደር መምሪያ በሚያወጣው መርሐ-ግብርና ዝግጅት ከቅዱስ ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያናችን በዓለ ሢመት አከባበር ጀምሮ ዓመታውያን ክብረ በዓላት በድምቀትና በሥርዐት እንዲከበሩ መደረጉ ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ክብርና ሞገስን አጐናጽፏል፡፡ ለወፊቱም ይህ የምእመናንን ትኩረት ጭምር የሳበ ዝግጅት ትኩረት ተሰጥቶት በትምህርት ሰጭነቱ ተፈላጊነት ያለው ስለሆነ እንዲበረታታ ጉባኤው ያስገነዝባል፡፡

    11. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ገዳማት የሕግና ሥርዐት ምንጮች፣ የአስተዳደራዊ ብቃት መገኛዎች፣ የቅርስና የንዋየ ቅድሳት ባለቤቶች መሆናቸው በሚገባ ይታወቃል፡፡

    በመሆኑም ገዳማት የታሪክ መዘክርነታቸው ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን የሚያበረክተው ጥቅም ከፍ ያለ ስለሆነ የገዳማት መምሪያው ተጠናክሮ በሁሉም ዘንድ ተገቢው ጥበቃና ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንጠይቃለን፡፡

    12. ሀ/ ልጆችና ወጣቶች የሀገርና የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ተረካቢዎች መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡

    የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እስከ አሁን ባለው እንቅስቃሴ የሚመሰገን ቢሆንም በሰንበት ት/ቤቶች ሥር ያልተደራጁትን በማሰባሰብ የማደራጀትና የማጠናከር ሥራውን እንዲቀጥል ጉባኤው አስገንዝቧል፡፡

    ለ/ በማኅበረ ቅዱሳን በኩል የሚደረገው ሐዋርያዊና የበጎ አድራጐት ሥራ መልካም ገጽታ የሚታይበት ስለሆነ ከመምሪያው ጋር በመግባባትና መመሪያን በመቀበል አገልግሎቱን እንዲቀጥል ጉባኤው ያሳስባል፡፡

    13. ሀ/ ገንዘብና ንብረት በአግባቡ በስሌት እየታሰበ ተመዝግቦ በጥንቃቄ ካልተጠበቀ፣ በበጀት ተወስኖም በማደላደል ካልተሠራበት፣ ገቢውና ወጭው ካልተመዛዘነ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ዕጥረትም ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለዚህም ድርጅታዊ መዋቅሩን አስተማማኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

    ስለዚህ እስከ አሁን የጠቅላይ ቤተ ክህነታችን በጀትና ሒሳብ መምሪያ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ በሒሳብ ሕግ መሠረት በቁጠባ እየያዘ የሰጠውና የሚሰጠው አገልግሎት የሚያስመሰግን መሆኑ ቢታወቅም ከዚህ በበለጠ አሠራሩን አጠናክሮ ቀልጣፋ የበጀት አጠባበቅንና በየደረጃው የማስተላለፍ ሥርዐቱን ከላይ እስከ ታች ይፈጽም ዘንድ ጉባኤው አጥብቆ ያሳስባል፡፡

    ለ/ የቤተ ክርስቲያኒቱ የገንዘብ ገቢ ሁሉ በወቅቱ ካልገባና ካዝናው ከጐደለ የሠራተኛውን መብት ጠብቆ ሥራ ለማሠራት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱንም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚጠበቅባትን ያህል ለመፈጸም አያስችልም፣

    ስለዚህ ፐርሰንት ከነውዝፉ ተጠቃሎ የሚገባበት የማስፈጸሚያ ስልትና መመሪያ በበጀትና ሒሳብ መምሪያ በኩል ወጥቶ ለሚመለከታቸው ሁሉ በአፋጣኝ እንዲተላለፍ በጉባኤው ተወስኗል፡፡

    ሐ/ በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ተመሳሳይና እኩልነት የሚታይበት አገልግሎትን በትክክል ለመፈጸም የበጀት ማእከላዊነት ቢኖር እንደሚበጅ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አጠቃላይ ሪፖርት የተገለጸውን ጉባኤው በአትኩሮት ተገንዝቦታል፡፡

    የካህናትንም ወደ አዲስ አበባ መምጣት ሊገታ ሰለሚችል ሐሳቡ በጉባኤው ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ በመሆኑም የአፈጻጸም ጥልቅ ጥናት ተደርጐ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ተግባራዊ እንዲሆን ጉባኤው አምኖበታል፡፡

    14. የገንዘብና የንብረት ቁጥጥር መጠናከር ለሀገርም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ምጣኔ ሀብት እድገት የወሳኝነት ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡

    በመሆኑም የቁጥጥር መምሪያው በበጀትና የሒሳብ ባለሙያዎች ተጠናክሮ የመቆጣጠሩን ተግባር እንደ አስፈላጊነቱ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤት ድረስ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው ያሳስባል፡፡

    15. በቅርስ ምዝገባና ጥበቃ መምሪያ አማካይነት ስለ ቅርሳ ቅርስና ንብረት አጠባበቅ ደንብ መውጣቱን፣ ቅርሶች በጥንቃቄ እንዲጠበቁም የተቀየሰውን ስልት፣ የተደረገውን ጥረትና የተወሰደውንም ሕጋዊ ክትትል ጉባኤው ተገንዝቦታል፤ አሁንም የቤተ ክርስቲያኒቱን የባለቤትነት መብት ከማስከበር ጋር በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ጥበቃው በሁሉም አህጉረ ስብከት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው የጠበቀ ዐደራውን ያስተላልፋል፡፡

    16. በጠቅላይ ቤተ ክህነታችን በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት መንፈሳዊ ፍትሕ ከአለፈው በላቀ ሁኔታ መስጠቱን ጉባኤው ከቀረበው አጠቃላይ ሪፖርት ሊገነዘብ ችሏል፡፡ ስለዚህ ፍትሕ ታላቅ ሥራ እንደመሆኑ መጠን መንፈሳዊ ፍርድ ቤቱ ተፈላጊው ሁሉ ተሟልቶለት ራሳችንን በራሳችን የመዳኘቱ ተግባር ከአሁን በበለጠ ፍሬው እንዲገለጽ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

    17. ማናቸውም ሥራ በአግባቡ ተከናውኖ ለውጤት ሊበቃ የሚችለው በጥናትና በዕቅድ ሲመራ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ በመሆኑም በማእከል ያለው የዕቅድና ልማት መምሪያ ከምሕንድስና ዘርፍ ጋር ተገናዝቦ ሥራዎች ሁሉ በባለሙያ ጥናት እየተመሠረቱ በማእከል በሚታወቅ ዕቅድና አምሳል መርገፍ/ፕላን/ እንዲሠራ ቢደረግ ከሕገ ቤተ ክርስቲያናችንና ትውፊታችን ወጣ ያሉ ግንባታዎች እንደሚገቱ ጉባኤው አምኖበታል፡፡

    18. በንዋየ ቅድሳት፣ በአልባሳትና ቅርጻ ቅርጽ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ኅትመትና ስርጭት ሥራ ላይ የተሠየሙ የቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሁሉ በዚህ በጀት ዓመት ትጋት ባልተለየው የራስ አገዝ እንቅስቃሴ የላቀ ውጤት ማሳየታቸውን ጉባኤው በአትኩረት ተገንዝቦታል፡፡

    ስለዚህ ከበላይ አካል የሚደረገው ክትትልና ማበረታቻ እንዳለ ሆኖ ድርጅቶቹ በራሳቸው ጥረትና የማስተዋል ጥበብ ምርቶቻቸውንና የስርጭት እንቅስቃሴያቸውን አብልጠው እንዲያጠናክሩ ጉባኤው በአክብሮት አሳስቧል፡፡

    19. እነዚህ በምርት ሥራዎች ላይ የተሰለፉ ድርጅቶቻችን በሙሉ ቤተ ክርስቲያንን በምጣኔ ሀብትና በሥራው ሁሉ ራሷን ለማስቻል ይራዱ ዘንድ ያረጁ የማምረቻ መሣሪያዎቻቸው በዘመናዊና በአዳዲስ እንዲለወጡ፣ ከምርት ድርጅቶቹ ግንባር ቀደም ጥናትና ማሳሰቢያ ጋር የበላይ አካልም እንዲያተኩርበት ጉባኤው ጠይቋል፡፡

    2ዐ. በቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት የተደረገው አስተዳደራዊ ለውጥና የታየው የገቢ እድገት ለጉባኤው ታላቅ ተስፋ ሰጥቶታል፡፡ ሕንጻዎችና ቤቶች አባቶቻችን በታማኝነትና ትጋታቸው ያቆዩን መታሰቢያዎች ከመሆናቸውም በላይ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ስለሆኑ ለወደፊቱም የተመለሱ ቤቶች ካርታ እንዲኖራቸው፣ ያልታደሱት ዕድሳት እንዲደረግላቸው፣ አነስተኛ ቤቶችም ደረጃውን በጠበቀ ሕንጻ እንዲለወጡ፣ በክፍት ቦታዎችም ግንባታ እንዲካሔድባቸው፣ ያልተመለሱት ቤቶቻችንም ጉዳይ በመልካም ውጤት እንዲጠናቀቅ፣ አህጉረ ስብከትን ሁሉ አካቶ ጥረቱ የበለጠ እንዲቀጥል ለድርጅቱና ለቤቶች አስመላሽ ኮሚቴው ከበላይ የአስተዳደር አካላችን ተገቢው የዘወትር ክትትልና የማበረታታት ተግባር እንዳይለየው ጉባኤው አጥብቆ ያሳስባል፡፡

    21. በብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ማስተዋል በተመላው አመራር የተቋቋመው የተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት ርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ አልባሳትንና ንዋየ ቅድሳትን ለተቸገሩ የገጠሪቱ አብያተ ክርስቲያናት ማከፋፈሉ እጅግ የሚያስመሰግነው ነው፡፡

    • ርዳታውን በገንዘብና በዐይነት የለገሱትን የዐዲስ አበባ ገዳማትና አድባራትም ጉባኤው በታላቅ ደስታ ያመሰግናል፡፡ ለወደፊቱም ይህ ምግባረ ሠናይ ማእከላዊ ክትትል ሳይለየው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዐደራ እንላለን፡፡

    22. በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስም እየተጠሩ ያለ ሕግና መመሪያ የሚንቀሰቀሱ ማኅበራት ሁሉ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የሚታቀፉበት፣ ወይም የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅዱስና ክቡር ስም ይዘው ከመንቀሳቀስ የሚገቱበት፣ በሚመለከተው ክፍል በኩል ሕጋዊ የሥራ ርምጃ ይወሰድ ዘንድ ጉባኤው አበክሮ ይጠይቃል፡፡

    23. ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን መስፋፋትና መጠናከር ኅብረተሰቡን በየቋንቋው ማስተማር ወሳኝነት እንዳለው ይታመናል፡፡

    ስለዚህ የመናፍቃንንም እንቅስቃሴ ለመግታት ስለሚደረዳ በካህናት ማሠልጠኞችና በኮሌጆቻችን በየቋንቋው የሚያስተምሩ ካህናት እንዲሠለጥኑ፣በአመዳደብ በኩልም፣ ትኩረት ያገኝ ዘንድ የበላይ አስተዳደራዊ መመሪያ እንዲሰጥ እናሳስባለን፡፡

    24. በግል የሥጋ ጥቅም ተታለው፤ ሃይማኖታቸውን ክደው፣ ክህነታቸውን ጥለው፣ ወደ መናፍቃን ጐራ የገቡ ካህናት መኖራቸው ስለተገለጸ ካህናት ሳይሆኑ የሆኑ እየመሰሉ ቀድሞ የሚያውቋቸውን ምእመናንን በስውር እንዳያታልሉ በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት ከተመከሩ በኋላ የማይመለሱ ሆኖ ሲገኝ ተገቢው ቀኖናዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ያስተላልፍ ዘንድ ጉባኤው በአጽንዖት ይጠይቃል፡፡

    25. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱን ሕግ አክብራ የእምነቷ ተከታዮች የሆኑትን ምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት፣ በሰላማዊ መንገድ እየመራች የራሷን ሥርዓተ አምልኮ በመፈጸምና በማስፈጸም ላይ እንደምትገኝ የታወቀ ነው፡፡

    ዳሩ ግን አንዳንድ አክራሪ ፀረ ቤተ ክርስቲያን አቋም ያላቸው ቡድኖች ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌና ከሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር ውጭ ሲፈታተኗት የሚታዩ ስለሆነ በቤተ ክርሰቲያኒቱ አንዳንድ አህጉረ ስብከት እየደረሰ ያለው ችግር ከመባባሱ አስቀድሞ ቅዱስ ሲኖዶስ ዘላቂ መፍትሔን እንዲፈልግ ጉባኤው በአጽንዖት ያሳስባል፡፡ ከዚህም ጋር መናፍቃንና ተቃራኒዎቻችን በአብያተ ክርስቲያናት ላይ አደጋን በማድረስ፣ ይዞታዋንም በመንጠቅ፣ በምእመናን ላይ ከሕግ ውጭ በተለያየ ስልት የሚያደረጉትን ትንኮሳ ሁሉ ለመግታት በየሀገረ ስብከቱ የተደረገው ትግል የሚደነቅ ነው፤ ነገር ግን ከበላይ የመንግሥት አካላት ጋር ምክክር ቢደረግ የመጨረሻ መፍትሔ እንደሚሆን ጉባኤው ያመነበት ስለሆነ ይኸው በሥራ እንዲገለጽ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የጠበቀ ዐደራውን ሰጥቷል፡፡

    26. አዳዲስ መንበረ ጰጵስናዎች ተጠናክረው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ሥራቸውን መወጣት እንዲችሉ ከራሳቸው ጥረት ጋር ከበላይ የሚደረገው ድጋፍ እንዲቀጥል፣ ራሳቸውን የቻሉ አቻ አህጉረ ስብከትም ትብብራቸውን እንዲያሳዩ ጉባኤው ከልብ ያስታውሳል፡፡

    27. በአገልጋዮች ዕጥረት አብያተ ክርስቲያናት እንዳይዘጉ ብዙ አገልጋዮችና የገንዘብ ዐቅም ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት በየሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አስተባባሪነት በወር ተራ ካህናትን የመላክ ሥራ ቢፈጸም፣ ለዘለቄታውም በካህናት አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በጋራ የጥናት ሐሳብ ለበላይ አካል እንዲቀርብ ጉባኤው መልካም ሐሳቡን ሰጥቷል፡፡

    28. ከሦስቱም ኮሌጆቻችን የሚመረቁ ደቀ መዛሙርት የመማራቸውን ዋና ዐላማ በውል ተገንዝበው በየተመደቡበት አህጉረ ስብከት በመሔድ ያለ ምንም ምክንያት አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ከማሳመን ሥራ ጋር አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ጉባኤው አጥብቆ ያሳስባል፡፡

    29. ሀ/ በቀድሞው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ እየተሠራ ያለው ከፍተኛ የሕክምና ማእከል፣ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን እየተሠራ ያለው ቤተ መጻሕፍት መወዘክር፣ በመንበረ ፓትርያርከ ጠ/ቤተ ክህነት ሊሠራ የታቀደው የተሟላ ዘመናዊ ሁለገብ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተጀምሮ ይፈጸም ዘንድ ጉባኤው በናፍቆት ይጠብቃል፡፡ ስለዚህ እኛ የጉባኤው አባላትም ለዚሁ ሥራ የበኩላችንን አስተዋፅኦ ለማድረግ በከፍተኛ ደስታ ቃል ገብተናል፡፡

    ለ/ በተመለሱ አሮጌ ቤቶችና ክፍት ቦታዎች ላይ ታላላቅ ሕንጻዎች እንዲገነቡ፣ የተያዘውና በአጠቃላይ በማእከላዊው ሪፖርት የተገለጹት ዕቅዶች በከፍተኛ ትጋት በሥራ እንደተረጐሙ ጉባኤው የጠበቀ ዐደራውን አስተላልፏል፡፡

    እኛም የጉባኤው አባላት በዚህ ዓመት በታየው መልካም እድገት ሳንዘናጋ የበለጠ ተጠናክረን ለመሥራት የሚያስችል ከልብ የማይጠፋ ግንዛቤን ከጉባኤው ያገኘን ስለሆነ ለበለጠው እድገት በርትተን ለመሥራት ቃል ገብተናል፡፡

    3ዐ. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊውን አገልግሎት በመስጠት ብቻ ሳትወሰን በማኅበራዊው አገልግሎት ዘርፍ ለሚደረገው ሀገራዊ እንቅስቃሴም ቀድማ የምትደርስ የኅብረተሰቡ አገልጋይ መሆኗ የሚታወቅ ነው፡፡

    ከዚህ ግንዛቤ በመነሣት ከአራቱ አፍላጋት አንዱ በሆነው ለታላቁ ዓባይ ወንዝ የሕዳሴው ግድብ አገልግሎት ይውል ዘንድ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከልነት ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤት ድረስ ከአሉት ሠራተኞች የተሰበሰበው ጠቅላላ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ገቢ መደረጉ ታውቋል፡፡

    ይህ ሀገራዊ ጥሪ በሁሉም አህጉረ ስብከት የተከናወነ ስለሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ የሚያስመሰገነ ነው፡፡

    31. ከትምህርተ ወንጌል ተልእኮ ውጤት አንዱ ኢ.አማንያንን ለጥምቀት ማዘጋጀት ስለሆነ በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት በጋምቤላ ሀገረ ስብከት በመገኘት የተለያየ እምነት ተከታዮች የሆኑትን የክልሉን ባለሥልጣናት በማጥመቅ የቤተ ክርስቲያናችን አባላት እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ጉባኤው በታላቅ አድናቆት ተመልክቶታል፡፡

    • ይህ አመርቂ ውጤት ሊገኝ የቻለው በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ያልተቆጠበ ጥረትና እንቅስቃሴ ስለሆነ በበጀት ዓመቱ የታየው የሥራ ፍሬ በእጅጉ ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡
    • በተመሳሳይነት በሌሎች አህጉረ ስብከትም የተለያየ እምነት ተከታዮች የሆኑ ሁሉ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው መመለሳቸውን የሚገልጽ በአብዛኛዎቹ አህጉረ ስብከት ሪፖርት ተነግሮ ተሰምቷል፡፡

    ስለዚህ 57ዐዐ የሌላ እምነት ተከታዮችን እንዳጠመቀው የከንባታ አላባ ጠንባሮ ሀገረ ስብከት አርአያነት ይህ በአዲስ አማንያን ዙሪያ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የስብከተ ወንጌልን እድገትና መስፋፋት የሚያመለክት ስለሆነ የትምህርተ ወንጌሉ ስርጭት በሁሉም አህጉረ ስብከት ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ጉባኤው ከልብ ያሳስባል፡፡

    32. በተለያየ ምክንያት ከውድ እናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ እየወጡ በሁሉም ክፍላተ ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛ ከመምጣቱ የተነሣ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጽሙበት፣ ሀብተ ወልድና፣ ስመ ክርስትና የሚያገኙበት፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲቋቋሙላቸው፣ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲመደቡላቸው የሚጠይቁ ምእመናን ብዙዎች ናቸው፡፡

    በተጓዳኝ መልኩም በውጭ ሀገር ላለችው ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ከተመደቡት መካከል የተወሰኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ሌሎችም ተወካዮች በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ማእከላዊ አስተዳደር ጥሪ አክብረውና ተቀብለው፣ አስፈላጊውን ፍሬ በረከት ይዘው፣ ሪፖርታቸውን አዘጋጅተው የጉባኤው ተሳታፊዎች ሁነው ለተገኙት የቤተ ክርስቲያኒቱ አለኝታዎች ጉባኤው ከፍተኛ ክብርና ሞገስ ሰጥቷቸዋል፡፡

    • በተለይም በደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ሀ/ስብከት ሪፖርት እንደተገለጸው በቅዱስነታቸው አመራር ሰጭነትና በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አስፈጻሚነት የቤተ ክርስቲያኒቱን ዓለም ዐቀፋዊ ይዘት አጉልቶ የሚያሳይ ብዙ ሥራ ተከናውኗል፡፡ ይህንም የሥራ ፍሬ በቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ጊዜ የተቀረጸው ፊልም በስክሪን ቀርቦ ጉባኤው በታላቀ አንክሮት ተመልክቶታል፡፡

    ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችንን በመላው ዓለም የማስፋፋት ተልእኮ ሁሉም የውጭ ሀገር አህጉረ ስብከት አጠናክረው መቀጠል ይችሉ ዘንድ ምልአተ ጉባኤው ዐደራውን ጥሎባቸዋል፡፡ በበኩላችንም ለዚህ ቅዱስ ዐላማ ስኬት እንዳለፈው ሁሉ የሚፈለግብንን ድጋፍ ለማበርከት ዝግጁዎች መሆናችንን እንገልጻለን፡፡

    በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላስተላለፈችው መንፈሳዊ ጥሪ ትኩረት ባለ መስጠት ይሁን በሌላ ምክንያት አብዛኞቹ በውጭ ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት በጉባኤው ላይ አልተገኙም፡፡ በአርአያነቱም ሆነ በምላሌነቱ ልዩ በሆነው በዚህ ዓለም ዐቀፍ ሠላሳኛው ጉባኤ በመገኘት አንድነትን አለመግለጽ ቅሬታን ከማሳደሩም በላይ ጥያቄን ሊያስከትል ስለሚችል ቅዱስ ሲኖዶስ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ አስፈላጊውን የማስተካከያ መመሪያና ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ጉባኤው በአጽንዖት ያሳስባል፡፡

    33. በሃያዎቹ ዓመታት የሥራ ዘመናት በተደረገው ታሪካዊ ጉዞ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ካስመዘገቧቸው በርካታ የሥራ ክንውኖች መካከል ዋና ዋናዎቹ ተቀርጸውና በዶክመንተሪ ፊልም ለእይታ ቀርበው ጉባኤው በአትኩሮት ተመልክቷቸዋል፡፡

    በፊልም የታየው መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተግባር የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተናዊ እድገት አጐልቶ የሚያሳይ የሚዳስስ ስለሆነ ቅዱስነታቸው በሁሉም አቅጣጫ የፈጸሙት ጉልህ የሥራ ተነሣሽነት ለሥራ ወዳዶች ሁሉ መልካም ምሳሌ መሆኑን በመገንዘብ አርአያነቱን ተከትለን ታሪክን በማቆየት የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

    ይኸው የቅዱስነታቸውን የሃያ ዓመታት ታሪካዊ የአገልግሎት ጉዞ የዘገባው ዶክመንተሪ ፊልም የታየበት ጊዜ አጋጣሚ ሆኖ በጉባኤው ላይ የተገኙት የፊዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር ዶክተር ሽፈራው ተክለ ማርያም በቅዱስነታቸው ዘመነ ክህነት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከልማት ዘርፍ ጀምሮ በሁሉም አቅጣጫ የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ በመመልከት አድናቆታቸውን ገልጸው ቅዱስነታቸው ሰላምን በማስፈን ረገድ ባደረጉት ፈጣን እንቅስቃሴ የሃይማኖት መሪዎቹን በማስተባበር "የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ" በሚል ስያሜ ሰላምን የሚያስተባብር አንድ ታላቅ የሰላም ጉባኤ መመሥረት እንደቻሉ አስረድተዋል፡፡

    ክቡር ዶክተር ሽፈራው ተክለ ማርያም ንግግራቸውን በመቀጠል ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶችን የሚከተሉ ሕዝቦች በእኩልነት የሚኖሩባት ሀገር እንደመሆኗ ከሃይማኖት ነጻነትና እኩልነት በስተጀርባ የፍራሽ ተልእኮ መልእክተኞች ቢየጋጥማችሁ ከዐላማችሁ ባለመናወጽ ትዕግሥትን ከጥበብ ጋር በማዋሐድ ስምምነት፣ ሰላምና ተከባብሮ በአንድነት መሥራት የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ባለመዘንጋት ትሠሩ ዘንድ ከፍተኛ ዐደራና ሓላፊነት ተጥሎባችኋል" በሚል ዘይቤ የሰጡትን ምክር አዘል መመሪያ ምልአተ ጉባኤው ተቀብሎታል፡፡

    በመጨረሻም የሰበካ ጉባኤ ማ/መምሪያ ይህ ዓለም ዐቀፍ ዐቢይ ጉባኤ በተሟላ ዘመናዊ ዝግጅነትና ቅንብር ውበትን ተላብሶ እንዲካሔድ ስላደረገው ትኩረት ጉባኤው ከፍ ያለ አድናቆትቱን እየገለጸ ወደፊትም በበለጠ መልኩ እንዲቀጥል ዐደራ ተጥሎበታል፡፡

    ማ ጠ ቃ ለ ያ

  • ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ሆይ!
  • ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጃችን፣
  • ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
  • የተከበራችሁ የጉባኤው አባላትና ተሳታፊዎች በሙሉ፣
  • "በበረከቶሙ ለራትዓን ትትሌዓል ሀገር= በነቢያት፣ በካህናትና በምእመናን የአንድነት ጸሎት ሀገር ታድጋለች፡፡ ከፍ ከፍም ትላለች፡፡" መጽ.ምሳ. 11፡11፣

    ይህ ቃል ሊቃውንት፣ ካህናትና ምእመናን በሰበካ ጉባኤ ተደራጅተው በሁለመናው እየተባበሩ የሚሠሩትና ወደ ፈጣሪያቸው በአንድ ሐሳብ የሚያቀርቡት ልባዊ ጸሎት ምን ያህል ለሀገር ልማትና እድገት እንደሚጠቅም የሚያስገነዝብ ሆኖ ይገኛል፡፡

    የአበው ነቢያትና ሐዋርያት ቃልና ንግግራቸው ሁሉ በግብር በማይገለጥ ሐሰት የደበሰ አይደለም፡፡ በዕለት ከዕለት ሥራችን በነቢያትና ሐዋርያት ቃል ከተመራን ዐደራና ሐላፊነታችንን ያለዕንከን እንወጣለን፡፡

    • በየማዕርጋችን በምድራዊት መንግሥቱ የተሾምን እኛ ሁላችን የአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዩች ነን፡፡
    • በቤተ ክርስቲያናችን ለመልካም እድገትና ልማት ከልባችን መነሣሣት ሀገራችን በአርአያነት የምትጠብቅብን ዐቢይ ቁም ነገር እንደሆነ ልንገነዘበው ይገባል፡፡
    • ጊዜያችን የሩጫና የሽቅድምድም ወቅት ነው፡፡ በዚህ ጊዜም ፈጥኖ መቅደም ይጠበቅብናል፡፡
    • የቤተ ክርስቲያናችን እድገት የማያስደስታቸው ቢጽ ሐሳውያን የሚያደርጉት እሽቅድምድምና ከሰመር የወጣ ትግል ሊያሳስበን ይገባል፡፡
    • የዚህ ማሸነፊያው ብቸኛ ዘዴም በፍቅር አንድነት ሰላምን መሥርተን ሕግና መመሪያን እያከበርን ሥራችንን በማሳመር መሥራት መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም፡፡ ለሀገርና ለወገን ጥቅም ሰበካ ጉባኤን የመሰለ ተቋም መሥርቶ ልማታዊ ሥራን በተባበረ ኅይል መሥራት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አምላክ ኃያሉ እግዚአብሔር የተገኘ አማናዊ ጥበብ ነው፡፡

    ስለዚህ ከቅዱስ አባታችን የተሰጠንን አባታዊ የሥራ መመሪያ፣ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተላለፈልንን ብርቱ ማስገንዘቢያ ተመርኩዘን ይህ ያቀረብነው የውሳኔ ሐሳብ፣ ያወጣነውም የጋራ አቋም መግለጫ ጸድቆ ሲተላለፍልን በሥራ ለመተርጐም የተናገርነው ሁሉ ቃለ ሃይማኖት ሆኖ እንደሚያስገድደን ያለ ጥርጥር እናምናለን፡፡

     

     

    ለዚህም የቅዱስ አባታችን ቡራኬ፣ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎት፣ የእመቤታችን ቅ/ድንግል ማርያም አማላጅነት ደርሶን፣ የሥራና ዋጋ ባለቤት እግዚአብሔር፣ አበው ሐዋርያትን በተራዳበት ኅይሉ እየረዳ እንዲመራን፣ ለበለጠ የሥራ ፍሬም እንዲያበቃን ቅዱስ ፈቃዱን እንለምናለን፡፡

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር