ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፤ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 25 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባን በማካሔድ፤

ሀ. ለቤተ ክርስቲያናችንና ለኅብረተሰቡ የሚጠቅመውን፤

ለ. ለሀገርና ለዓለም ሰላም የሚበጀውን አጀንዳ በማመቻቸት በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል፡፡

1. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና በየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ካህናት የቀረበውን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሪፖርት መርምሮ በማጽደቅ ካለፈው በበለጠ መሥራት የሚያስችል መመሪያን ሰጥቷል፡፡

2. ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በልማት ዘርፍ ዙሪያ የምታደርገው እንቅስቃሴ በማዕከልም ሆነ በየአህጉረ ስብከቱ በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፤

3. በውጭ ሀገር ራሳቸውን ሕጋዊ ሲኖዶስ እያሉ ከሚጠሩት አባላት ጋር ተጀምሮ የነበረው የዕርቀ ሰላም ድርድር ጉዳይ በሰሜን አሜሪካ በአሪዞና እስቴት ፊኒክስ ከተማ ይቀጥል ዘንድ ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፤

4. የአብነት ትምህርት ቤቶችንና የካህናት ማሠልጠኛ ማዕከላትን፤ በጥንታዊነታቸውና በታሪክ መዘክርነታቸው ዕውቅና ያላቸውን ገዳማት፤ ወላጅ አልባ ዕጓለማውታ ሕፃናት እየተማሩ የሚያድጉበትንና ሴቶች መነኰሳይያት በምናኔ የሚኖሩባቸውን ገዳማት በበለጠ እንዲጠናከሩ ማድረግ የታመነበት ስለሆነ፤ ለዚሁ አገልግሎት የሚውል በጀት በቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕከላዊ አስተዳደር ተጠንቶ ይቀርብ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያን ሰጥቷል፤

5. የ2004 ዓመተ ምሕረትን በጀት አጠቃቀም በተመለከተ፤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የቀረበው የሒሳብ ዝርዝር መግለጫ ሪፖርት ከተመረመረ በኋላ ከገቢው አንፃር የወጭው ጣሪያ ተጠብቆ እንዲሠራበት ተወስኗል፤

6. ቀደም ሲል በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሥር የነበረውን መንፈሳዊ ፍርድ ቤት በአዲስ መልክ ለማቋቋም ተዘጋጅቶ የቀረበው የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በቅዱስ ሲኖዶስ ከታየ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቅ ዘንድ ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፤

7. የዓለምን ሰላም፤ ፍቅር አንድነትን ጠብቆ መገኘት የሁሉም ኃላፊነት ስለሆነ ሁሉም ኅብረተሰብ አነድነትን ፈጥሮ ሰላምን የማስፈን ግዴታውን እንዲወጣ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች

8. የእናቶችና የዕጓለማውታ ሕፃናት፣ የአረጋውያንና የአረጋውያት፤ የሁሎችም ፍላጎት ተሟልቶ መኖር ይችል ዘንድ ኅብረተሰቡ ትኩረት እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፤

9. ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት፤ አገልግሎት የሚውል ቦንድ እየገዙ እንዲያበረክቱ ቀደም ሲል በተሰጠው መመሪያ መሠረት በሁሉም አህጉረ ስብከት ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ መንበረ ፓትርያርክ ባለው መዋቅር እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያን ሰጥቷል፤

10. ሀገራችን ኢትዮጵያ ከኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ፣ ከድንቁርና፣ ከድኅነትና ኋላ ቀርነት ተላቃ ዓለም ወደ ደረሰበት መድረስ የምትችለው ማንኛውም ወገን ተቻችሎና ተከባብሮ ለሰላምና ለልማት ሥራ ሲነሣሣ ስለሆነ፤ ይኸው ታውቆ ሁሉም የየበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

11. ከሀገራችን ውጭ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ተመድበው ከሚሠሩት መካከል የተወሰኑ ሊቃነ ጳጳሳት በሀገር ውስጥ ተመድበው እንዲሠሩ፤ በሀገር ውስጥ ካሉትም መካከል የሥራ ዝውውር እንዲደረግላቸው ጥያቄን ያቀረቡ ሊቃነ ጳጳሳት ተዛውረው ይሠሩ ዘንድ ዝውውሩ ተፈቅዶላቸዋል፤

12. በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል የተፈጠረው የሥራ አለመግባባትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ አለ የተባለው ችግር፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የተመረጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሚገኙበት ስብሰባ፤ በሊቃውንት ጉባኤ አማካይነት ተጣርቶ ይቀርብ ዘንድ ምልዓተ ጉባኤው መመሪያን ሰጥቷል፤

13. በ1991 ዓ.ም. ተሻሽሎ እየተሠራበት የቆየው ቃለ ዓዋዲ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ፤ አሁንም እንዲሻሻል በቀረበው ጥያቄ መሠረት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሚገኙበት ኮሚቴ ለሦስተኛ ጊዜ ተጠንቶና ተሻሽሎ ይቀርብ ዘንድ ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፤

14. የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አስተዳደር ጉዳይ በተመለከተ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕከላዊ አስተዳደር ተዘጋጅቶ የቀረበው ጥናታዊ መግለጫ፤ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የሕግ ባለሙያዎች ከተጠና በኋላ ለቅዱስ ሲኖዶሱ የ2004 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ጉባኤ እንዲቀርብ ምልዓተ ጉባኤው መመሪያን ሰጥቷል፤

15. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በርካታ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ጥበብ፣ ሥነ ሥዕልና ኪነ ጥበብ ቅርሶችና ሀብቶች ባለቤት መሆንዋ የታወቀ ስለሆነ፤ የእነዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱ የዜማ መጻሕፍት፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ የሕንፃዎች፣ የቋንቋ በአጠቃላይም ብሔራዊው የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብቷ በሕግ ይከበር ዘንድ በቅርስ ጥበቃና ምዝገባ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ተከታታይነት ጉዳዩ ለሚመለከተው የፍትሕ አካል ቀርቦ ውሳኔን እንዲያገኝ፤

16. ለሁሉም ጊዜ አለው እንደተባለው ሁሉ የተወሰደው ከተመለሰ፤ ስደተኛው የዓባይ ውሀ ተገድቦ ሀገሩን እንዲያለማ ከተደረገ፤ አዳዲስ የባቡር ሐዲድ በየአቅጣጫው ከተዘረጋ፤ የአስፋልት መንገዶች በከተማና በገጠር በሁሉም አቅጣጫ ከተሠሩ፣ ሌሎችም የተሰረቁ፣ የተዘረፉ እንደዚሁ እንደሚመለሱና የወደቀውም ሐውልታችን ተመልሶ እንደሚቆም መንግሥታችን እያደረገ ያለውን ጥበብ የተመላበትን ጥረት ምልዓተ ጉባኤው ተመልክቶ አድናቆቱን ገልፃDል፤ የበኩሉንም ድርሻ ለመፈጸም ተስማምቷል፤

17. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕውቅናን ያልሰጠቻቸው ሰባክያንና ዘማርያን ነን ባዮች ከሚያደርጉት ኢ-ሕጋዊ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ ምልዓተ ጉባኤው ውሳኔን ሰጥቷል፡፡

18. በጥንታዊቷ፣ በታሪካዊቷ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ከሃያ አምስት ሚሊዮን ዩ.ኤስ. ዶላር በላይ በሚሆን ወጭ እየተገነባ ያለውን የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሥራ ለማፋጠን፤ በታሰበው ጊዜና ወቅት እንዲሳካ፣ እንዲደመደም ለማድረግ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩት፤ - ኢትዮጵያውያን፤ - ኢትዮጵያውያት፣ - ርዳታን አድራጊ ለጋሽ ድርጅቶችና የመሳሰሉት ሁሉ የርዳታ እጃቸውን ይዘረጉ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ በተገለፁትና በሌሎችም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ለዐሥራ አምስት ቀናት ያህል ሲወያይ ሰንብቶ አስፈላጊውን በመወሰን መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት በጸሎት አጠናቋል፡፡

ቸሩ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን፣ ለሕዝባችን፣ ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ምሕረቱንና ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን ፡፡

እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ አሜን ፡፡

አባ ጳውሎስ (ዶክተር) ቀዳማዊ ፓትርያርክ

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት

የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም

የክብር ፕሬዚዳነት

ጥቅምት 25 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም.