ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያና ግብፅ በአሁኑ ወቅት ስላላቸው ግንኙነት አዲስ ሒደት በማጠናከር ዙሪያ ከግብፁ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አሳም ሸሪፍ ጋር ተወያዩ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዝዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት፣ በግብፅ ባካሔዱት የ4 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከተለያዩ የአገሪቱ የመንግሥትና የሃይማኖት መሪዎች ጋር ተወያይተዋል ፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ከግብፁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አሳም ሸሪፍ ጋር ባካሔዱት ውይይት እንደተናገሩት ግብፅና ኢትዮጵያ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ግንኙነት ያላቸውና ግንኙነቱም ለ16ዐዐ ዓመታት የዘለቀ መሆኑን አውስተው በዓለም እንደ ሁለቱ አገራት የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት አለመኖራቸውን ተናግረዋል ፡፡

ይህን የዘመናት መልካም ግንኙነት የሁለቱም አገሮች መሪዎች በመከባበርና በመግባባት ተቀራርበው በመነጋገር ሊጠብቁት እንደሚገባ አስረድተዋል ፡፡

የሁለቱ ሀገራትና አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት በአዲስና መልካም ሒደት ላይ መሆኑንም እንዳስደሰታቸው ቅዱስ ፓትርያርኩ ገልፀውላቸዋል ፡፡

ውይይቱን የተከታተሉት በግበፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር መሀመድ ድሪር እንዳሉት የአባይ ወንዝ ሁለቱን ህዝቦች የሚያስተሳስር እንጂ የሚያቀያይም አለመሆኑንና በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ ህዝቦችዋን የሚጠቅም እንጂ ማንንም የሚጐዳ አለመሆኑን ሁሉም ግብፃዊ ሊረዳው የሚገባ ሀቅ መሆኑን መናገራቸውን አስረድተዋል ፡፡

የግብፁ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አሳም ሸሪፍ በበኩላቸው በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ የግበፅ ህዝብን በቀጥታ ይጐዳል የሚሉት አካላት የሁለቱም አገሮች የቆየ ግንኙነት እንዲቀጥል የማይፈልጉና የኢትዮጵያን ዕድገት የሚጠሉ መሆናቸውን አብዛኛው የግብፅ ህዝብ ተገንዝቧል ብለዋል ፡፡

ሁለቱም አገሮች ለጋራ ዕድት መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል ፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ የግበፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን አቻቸው የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ 4ዐኛ በዓለ ሲመት በዓል ላይ ተገኝተዋል፡፡ የ88 ዓመቱ የግብፅ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ የግብፅ 117ኛ ፓትርያርክ ናቸው ፡፡

በዚሁ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፖፕ ሽኖዳ ላለፉት ዓመታት ለሰላምና ለልማት ያደረጉትን አገልግሎት ካወሱ በኋላ ረጅም ዕድሜና ጤና ተመኝተውላቸዋል ፡፡

የሶሪያና የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርኮችም በዚሁ በዓል ላይ ተገኝተዋል ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከግብፅ የእስልምና ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አዛር ሼክ አህመድ አልጠይብ ጋር ተገናኝተው ተነጋርረዋል ፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ እንደገለፁት በዓለም የሚታየው ግጭትና የሰላም እጦት በእውቀት ማነስና አንዳችን ሌላውን ለመቀበል አለመፈለግ መሆኑን ተናግረዋል::

 

የሁለቱ ሃይማኖቶች ተከታዮች ለሰላምና ለጋራ ልማት በጋራ የመሥራት፣ የመተሳሰብና የመቻቻል ኃላፊነት አላቸው ብለዋል ቅዱስ ፓትርያርኩ ፡፡ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው እንዳሉት በእስልምና አስተምህሮት የኢትዮጵያ መልካም ተግባር እየታወሰ እንደሚኖር ገልፀዋል ፡፡