በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !

• በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፤

• ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፤

• የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤

• በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤

• እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት

ሰማይንና ምድርን፣ በውስጣቸው የሚገኙ ፍጥረታትን የሚታዩትንና የማይታዩትን የፈጠረ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከዘመነ ሉቃስ 2ዐዐ3 ወደ ዘመነ ዮሐንስ 2ዐዐ4 ዓ.ም. በሰላም አደረሳችሁ ፡፡

"ዘይሔድሳ ለምድር በበረከቱ"?

"እግዚአብሔር አምላክ ምድርን በበረከቱ ያድሳታል /ድጓ/"

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እኛም እንደምንገነዘበው እግዚአብሔር አምላክ በፍጡራን አእምሮ ሊመጠን በማይችል በረከቱ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ በማያቋርጥ ሒደት እያደሰ ይኖራል ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረታት እየታደሱ እንዲተካኩ በማድረጉ የቀደመው ሲያልፍ አዲሱ ሲተካ የሕይወት ጉዞ የማያቋርጥ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎአል ፡፡ ከጌታችን ከአምላካችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው አሮጌ ዘመን ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኩነኔ በእርሱ መሥዋእትነት ሲያሳልፍ ከልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ያለውንም የምሕረት ዘመን ብሎ አድሶታል ፡፡ ወደፊትም በዳግም ምጽአቱ ሰማይንና ምድርን በማሳለፍ የተሻለ ሕይወት ለሰው ልጆች መስጠቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ከቅዱስ ወንጌል ተምረናል ፡፡ (ማቴ. 24-25) በመሆኑም ፍጥረታትን የማሳለፉ ተግባር የእግዚአብሔር ቀዋሚ ሥራ ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በባህርዩ ማርጀትና ኅልፈት የሌለበት ነው፤ በመጻኢው ዓለም ለሰው ልጆች ያዘጋጀው ሕይወትም ማርጀትና ኅልፈት የሌለበት፣ ሁል ጊዜ ሐዲስ ሆኖ የሚኖር ነው፡፡ የሃይማኖታችን ጽኑ ተስፋም በአዲሱ ዓለም ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይሁንና ወደ አዲሱ ዓለም ለመድረስ በየዘመኑ አዳዲስ ሥራዎችን በመሥራት እግዚአብሔርንና ፍጡራኑን በትጋት ማገልገል ያስፈለጋል፡፡ በዚህ ዓለም በፍጡራን ዓቅም ሊታደስ የማይችል ነገር ቢኖር ሃይማኖት ብቻ ነው፡፡ ከሃይማኖት በቀር ሌላው ሁሉ ለሰው ልጅ በሚጠቅም መንገድ ሊሻሻል፣ ሊስተካከልና ይበልጥ ሊጠቅም የሚችልበትን ዘዴ ተከትሎ ማሻሻል ተገቢ ይሆናል ፡፡ ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመን ከተቆጠረ አንሥቶ እስካሁን ባለበት ብቻ ቆሞ የኖረበት ዘመን የለም፤ በየጊዜው አዳዲስ የአሠራር ስልቶች እየተፈጠሩ፣ በቀጣይም በሌላ አዲስ ስልት እየተተኩ ይኖራሉ፤ ይህም ቀዋሚ የሆነ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው ፡፡ ከዚህ አኳያ በተሰናባቹ በ2ዐዐ3 ዓመተ ምሕረት ማብቂያና በአዲሱ 2ዐዐ4 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ቆም ብለን ልናስበው የሚገባ ነገር አለ ፡፡ ይኸውም በተሰናባቹ ዓመት የነበረንን አጠቃለይ ሥጋዊና መንፈሳዊ ተግባር መመርመር ሲሆን ያልሠራንባቸው አጋጣሚዎች ካሉም በአዲሱ ዘመን አካክሰን በመሥራት ያመለጠንን ሁሉ በእጥፍ ሠርቶ ለመተካት ጠንክሮ መሥራት ያስፈለጋል ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ

አዲሱ ዓመት ሲመጣ የደስታና የብልጽግና ዘመን እንዲሆንልን ከመመኘቱ ጋር በብሩህ ተስፋ መቀበላችን መልካም ነው፤ ይሁንና የደስታና የብልጽግና ምኞታችን ወደ ተጨባጭ ፍሬ ሊደርስ የሚችለው በሥራ ብቻ ነው ፡፡ በዓለማችን፣ እንዲሁም በአካባቢያችን የምናያቸው ውብና ድንቅ ነገሮች ሁሉ የሥራ ውጤት መሆናቸውን ለአንድ አፍታ እንኳ ቢሆን ልንዘነጋው አይገባም ፡፡ እግዚአብሔር እኛን የፈጠረ ለሥራ እንጂ ለሌላ አይደለም፤ በሥራ ላይ ቸልተኛነትን የምናሳይ ከሆነ ኑሮአችን መመሰቃቀል ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት መክሊት ቀባሪ ተብሎ መጠየቅም እንዳለ ማሰብ ይገባናል ፡፡ እንደሚባለውም ‹‹ሰው ለመብላት አይኖርም፤ ለመኖር ይበላል እንጂ፤ እንዲሠራ፡፡››አባ ጳውሎስ ዶክተር ቀዳማዊ ፓትርያርክ

ለሥራ ክብርን አለመስጠት፣ እግዚአብሔር እኛን የፈጠረበትን ዓላማ እንደመዘንጋት የሚያስቆጥር ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ለእኛ የሚበጅ አይደለም ፡፡ (ዘፍ. 1፡3) እግዚአብሔር ከበረከቱ ያጎደለብን አንዳችም ነገር የለም፤ በየጊዜው አዲስ የሆነ ራዕይ፣ አዲስ የሆነ አሠራር፣ አዲስ የሆነ ጥበብ፣ አዲስ የሆነ ዘመን፣ አዲስ የሆነ ጤንነት ወዘተርፈ ከመስጠት ያቋረጠበት ጊዜ የለም ፡፡ ይሁንና እርሱ የሰጠንን አዲስ የዘመን ስጦታ በአዲስ አስተሳሰብና አሠራር ተቀብለን ካልተጠቀምንበት አዲስ ዘመን ማለቱ ብቻ ከምኞትና ከቃላት ያለፈ ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡ ዘመኑ አዲስ ሊሆን የሚችለው እኛ በምናበረክተው ሥራ እንጂ ዘመን በራሱ አዲስ ሊሆን አይችልምና እግዚአብሔር አምላክ የሚወዳችሁና እግዚአብሔርን የምትወዱ ልጆቻችንና ወገኖቻችን በሙሉ አዳዲስ ሥራዎችንና አሠራሮችን በመፍጠር አዲሱን ዓመት በሁለመናው አዲስ አድርገን እናክብረው ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን እየጎለበተ፣ እያደገ የመጣው የሕዝቦቻችን የእርስ በእርስ መከባበርና መተማመን፣ በአንድነትና በስምምነት ለአንዲት ሀገር ሁለንተናዊ ልማትና እድገት በጋራ መነሣሣት ለብልጽግናችን የማይናወጥ መሠረት መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ በተለይም ሀገራችን ዛሬ የጀመረችውን የዕድገት መርሐ ግብር የድኅነታችን መቋጫ የብልጽግናችን ማረጋገጫ እንደሚሆን በማመን፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አምነው የጀመሩትን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ እስከ መጨረሻው ድረስ ያለመታከት ለስኬታማነቱ እንዲረባረቡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ፡፡ የሕዝባችንን ኅብረት፣ ስምምነት፣ መከባበርንና መተማመንን አስከብሮና የተጀመረውን የልማት መርሐ ግብር አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ ድኅነትን ከሀገራችን ነቅለን ታሪክ ለማድረግ ብዙ ጊዜ እንደማይወስድብን ጅምሮቻችን እያመለከቱን ነውና በዚሁ በርትተን እንድንቀጥል አባታዊ መልእክታችንን በአጽንኦት እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የሥራ ዘመን ያድርግልን !!

እግዚአብሔር አምላካችን ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ አሜን!!

አባ ጳውሎስ ዶክተር ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም፣

ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት

መስከረም 1 ቀን 2004 ዓ.ም