ህዝቡ ቅርሶቹን መንከባከብና መጠበቅ እንደሚገባው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አስገነዘቡ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት በርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን በመሰራት ላይ ያለው ሙዚየምን ከጎበኙ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለጥንታዊ ቅርሶች ህልውናና ደህንነት መጨነቅና በዘመናዊ ሙዝየም ተሰባስበው የሚቀመጡበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባዋል ብለዋል ፡፡
ይህን ቪዲዮ ይመልከቱ
ጥንታዊያን ቅርሶቻችን የማንነታችን መገለጫ ብቻ ሳይሆኑ ለሀገራችን ገጽታ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆናቸው ቅርሶቻችንን በሚገባ ሁኔታ ማስቀመጥ፣ በተደራጀና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማስጐብኘት ይገባል ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ ዘመናዊ ሙዝየም በመገንባትና ለጐብኚዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠርም ገጽታችንን የበለጠ መገንባትና ከጐብኚዎች በሚገኘው ገቢም ድህነትን መዋጋት ይቻላል ብለዋል ፡፡
በማያያዝም በአክሱም ከተማ የሚገኙ ጥንታዊያን ቅርሶችና ሃውልቶች የሥልጣኔያችን ቋሚ ምስክሮች በመሆናቸው ደህንነታቸው አስተማማኝ በሚሆንበት መልኩ መጠበቅ ይገባቸዋል ካሉ በኋላ እነዚህ ጥንታዊያን ቅርሶችን በሚገባ ሁኔታ በመንከባከብና በመጠበቅ ለታሪክ ተመራማሪዎች፣ ለጐብኚዎችና ለተማሪዎች ምቹ ማድረግ ይቻል ዘንድም ቤተክርስቲያኒቱ ደረጃውን የጠበቀ ሙዝየም ከ8.9 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በሆነ ወጪ በአክሱም ከተማ እያስገነባች ነው ብለዋል ፡፡
የአክሱም ጥንታዊያን ቅርሶችን በሚገባ መልኩ ለማስቀመጥ በአክሱም ጽዮን በመገንባት ላይ ያለው ሙዝየም የመላው ኢትዮጵያዊያን ስለሆነ ለሙዚየሙ ግንባታ ሁሉም ህዝብ መረባረብ እንደሚገባው ፓትርያርኩ ገልፀዋል ፡፡
የሙዝየሙ ግንባታም 17 በመቶ መከናወኑን ለማወቅ ተችሏል ፡፡

በአክሱም ጽዮን የሚገነባው ሙዝየም ቅርሶችን በሚገባ መልኩ አደራጅቶ የሚይዝ ከመሆኑም በላይ እያንዳንዱን ቅርስ ከስርቆትና ከብልሽት መጠበቅ የሚያስችል ዘመናዊ ሜካኒካልና ኤሌክትሪካል መሣሪያ ስለሚገጠምለት ለቅርሶቹ ደህንነት እጅግ አስተማማኝና ወሳኝ እንደሚሆን ይታመናል::
የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ ቤተክርስቲያኒቱ የአክሱም ቅርሶችን መጠበቅና መንከባከብ ይቻል ዘንድ ዘመናዊ ሙዝየም ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት አድንቀው የክልሉ መንግሥት ለግንባታው መፋጠንና መጠናቀቅ ድጋፍና አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ፡፡
ይህን ቪዲዮ ይመልከቱ
ህዳር 21 ቀን 2004 ዓ.ም




